በ38ተኛ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጥቅምት 23/2015 ዓ/ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተከናወነው የሰላም ስምምነት ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትኤ የሚለው እሳቤ በተግባር የተረጋገጠበት መሆኑ ተገልጿል፡፡
አጠቃላይ የሠላም ስምምነቱ ሒደት እና የአህጉሪቱ አገራት እንዲሁም ህብረቱ ከዚህ ስምምነት ምን ሊማሩ ይገባል የሚሉ ነጥቦች የተካተቱበት ሪፖርት ትላንት በህብረቱ ጉባኤ ቀርቧል፡፡
ለሰላም ስምምነቱ ስኬት የኢ.ፌ.ደ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያበረከቱት አስተዋጽኦ እና ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚያስመሰግን ነው ተብሏል፡፡
በአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች የሠላም እና ደህንነት ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር ሌሎች የአፍሪካ አገራት ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሊማሩበት ይገባል ብለዋል፡፡ አንዱ የስኬቱ ቁልፍ ነጥብ የአመራር ቁርጠኝነት መሆኑንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
ለፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ትግበራ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሚና ከፍተኛ እንደነበርም ነው የተናገሩት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የሰሜኑን የሠላም ችግር ወደ ሌሎች አገራት፤ ተቋማት ወይም መሪዎች ሳይወስዱ አፍሪካዊ ችግር በአፍሪካዊያን ነው መፈታት ያለበት በሚል እሳቤ ወደ ህብረቱ ማምጣታቸውን፤ እንዲሁም ከጅምሩ አንስቶ ለስኬቱ የነበራቸውን ሚና ኮሚሽነሩ አድንቀዋል፡፡
የአንድ አገር ልጆች የሆኑት ሁለቱም ቡድኖች ችግሮቻቸውን በአፍሪካ ጥላ ስር ተወያይተው በመፍታታቸው ምስጋና ይገባቸዋል፤ ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ህብረት መውሰድም ትልቅ ስትራቴጂ ነው ብለዋል፡፡ ተሰናባቹ የአፍሪካ ህብረት ኮምሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሃማት በበኩላቸው የሰሜኑን ጦርነት ለመፍታት የተደረገው የሰላም ንግግር በኢትዮጵያ ትልቅ ውጤት ያመጣ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡
አጀንዳ 2063 እ.ኤ.አ በ2030 የጥይት ድምጽ የማይሰማባትን አፍሪካ እውን ማድረግ አንዱ ግቡ ቢሆንም ይህን እቅድ ለማሳካት አገራቱ ብዙ ርቀት አልሔዱበትም ብለዋል፡፡ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ትልቅ ትምህርት ሊወሰድበት እንደሚገባም አጽዕኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ህብረቱ ካሳካቸው ስኬቶች መካከል አንዱ በመሆኑ ለሌሎች ማስተማሪያነት ተሰንዶ እንደሚቀመጥም ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በዚሁ መድረክ ባደረጉት ንግግር ጥቅምት 23/2015 ዓ/ም በፕሪቶሪያ ለተደረገው የሠላም ስምምነት በተለያየ መልኩ አበርክቶ ለነበራቸው አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ