በኢትዮጵያ የሚጥል በሽታ መድሐኒት እጥረት መኖሩን ኬር ኢፕሊብሲ ኢትዮጵያ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው ያስታወቀው፡፡
የበሽታው ታማሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢሆንም ከፍተኛ የመድሃኒት አቅርቦት እጥረት እንዳለ የኬር ኢፕለብሲ ኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ አቶ አቢይ አስራት ለጣቢያችን ገልጸዋል።
ሀገር ውስጥ ያሉት መድሃኒቶች በአይነት ከ4 እንደማይበልጡ የሚገልጹት ስራ አስኪያጁ፣ እነሱም ቢሆኑ ባለፉት አምስት አመታት በጸጥታ ችግር ምክንያት በአግባቡ አለመሠራጨታቸውን ነው የተናገሩት።
አብዛኞቹ ለሚጥል በሽታ የሚያገለግሉ መድሃኒቶች ከውጭ የሚገቡ መሆኑን የሚገልጹት ስራ አስኪያጁ፣ በአንጻሩ አብዛኛው ታማሚዎች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ በመሆኑ ውድ ዋጋ ያላቸውን መድሃኒቶች ገዝተው መጠቀም እንደማይችሉ አስረድተዋል። በመሆኑም የጤና ሚኒስቴር ለችግሩ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
ከመድሃኒት እጥረቱ በተጨማሪ ለሚጥል በሽታ የሚሆን በቂ የህክምና አቅርቦት አለመኖሩን ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
የበሽታውን አሳሳቢነት እና የታማሚውን ብዛት የሚመጥን በቂ የህክምና አሰጣጥ ስርዓት አለመኖሩን የሚገልጹት ኃላፊው፣ ዘርፉ ከፍተኛ የባለሙያ እጥረት አለበት ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው የግንዛቤ ክፍተት ትልቁ ተግዳሮት እንደሆነ ነው የተናገሩት። ማህበረሰቡ በሽታውን ከባእድ አምልኮ እና እርግማን ጋር በማያያዝ ታማሚዎች ዘመናዊ ህክምና እንዳያገኙ ይደረጋል ብለዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ ስርጭቱ እየጨመረ ላለው የሚጥል በሽታ በጤና ሚኒስቴር በኩል እየተሻሻሉ ያሉ አሰራሮች ቢኖሩም ቀደም ሲል የተገለጹ ችግሮች አሁንም ተግዳሮት ሆነው መቀጠላቸውን ስራ አስኪያጁ አመላክተዋል።
ምላሽ ይስጡ