የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በቅርቡ አራት አዳዲስ ቅርንጫፎችን ወደ ስራ ሊያስገባ መሆኑን ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡
አሁን ላይ ተቋሙ አገልግሎት እየሰጠበት ያለው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ የሚገኘውን ዋና ቢሮ ወደ ጎተራ ወንጌላዊት ህንጻ አከባቢ የቀየረ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ በመዲናዋ በአራቱም ማዕዘናት አገልግሎት የሚሰጡ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተደራጁ ቅርንጫፎቹን ስራ እንደሚያስጀምር የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳሬክተር ወ/ሮ ሠላማዊት ዳዊት ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ አገልግሎቱ በአንድ ማዕከል የተወሰነ በመሆኑ በርካታ ሰዎች ለእንግልትና ለመጭበርበር እየተዳረጉ ሲሆን ፤ አራቱ አዳዲስ ቅርንጫፎች ወደ ስራ ሲገቡ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ይቀረፋሉ የሚል እምነት እንዳላቸው በትላንትናዉ እለት ድንገተኛ ጉብኝት በተቋሙ ላደረጉት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ዳሬክተሯ አስረድተዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ተቋሙ በቅርቡ ወደ ስራ የሚያስገበውን አዲስ የፓስፖርት አይነት ማዘጋጀቱን የኢሚግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጎሳ ደምሴ ተናግረዋል፡፡
ቀደም ባሉት ጊዜያት የኢትዮጵያ ፓስፖርት ዲዛይን በግለሰቦች እጅ እንደነበረ በማመላከት አሁን ላይ በተቋሙ ዲዛይን የተደረገ በርካታ የደህንነት መለያዎች የተካተቱበት ፓስፖርት በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡
ተቋሙ የቀድሞ ቦታውን እስከ ሰኔ 2017 ዓ.ም ብቻ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረጉን የገለጸ ሲሆን አዲስ ቅርንጫፎቹ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፤ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፤ አቃቂ ቃሊቲና ኮልፌ ክፍለ ከተማ መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡
ምላሽ ይስጡ