የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የብድር አሰጣጥና አመላለስ ላይ በቀረበው ኦዲት በተሰጡ ሃሳቦች ላይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሊማርበት እና በተሰሩ አዎንታዊ ስራዎች ደግሞ ማሻሻያ ሊያደርግባቸው እንደሚገባ አስገንዝቧል።
ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የብድር አሰጣጥና አጠቃቀም ስርዓት ላይ ከፌደራል ኦዲተሮች ከልማት ባንክ አስረጅዎች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
ውይይቱ የተካሄደው የፌዴራል ኦዲተር ጄኔራል በ2015/16 በጀት ዓመት ባካሄደው የኦዲት ግኝቶች ላይ ተመርኩዞ ነው።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሽመቤት ደምሴ ( ዶ/ር) እንዳሉት ምንም እንኳን በ2014 የዘርፉ ፖሊሲ ቢሻሻልም፣ የልማት ባንኩ የፖሊሲ ማስፈጸሚያ መመሪያ የሌለው መሆኑን ጠቁመው፣ ይህን ፖሊሲ መሰረት ያደረገ መመሪያ እስከ የካቲት 30 ፀድቆ ወደ ስራ መግባት እንዳለበት አሳስበዋል።
በተጨማሪም ባንኩ የተበዳሪዎችን ማንነት ከገቢዎችና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር ማረጋገጥ እንደሚገባው አስረድተዋል።
ልማት ባንኩ ስራውን ለሚሰራው አካል ተግባር ተጠያቂነትን በሚያሰፍን መልኩ ስራውን በአግባቡ ሳይሰራ ሲቀር ሊጠየቅ የሚችልበትን አግባብ አስቀምጦ መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሰረት ሃይሌ የልማት ባንክ የማምረቻ ብድር አሰጣጥና አመላለስን በተመለከተ ኦዲት ሲያደርጉ 3 የትኩረት አቅጣጫዎችን አስቀምጠው እና አርባ አራት መስፈርቶችን በመለየት ኦዲቱን ከ 2013-2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ድረስ ማካሄዳቸውን ገልጸዋል።
ባንኩ በርካታ ሪፎርሞችን አካሂዷል ነገር ግን ለወደፊቱ የበለጠ ውጤታማ ሆኖ እንዲሄድ ከተፈለገ የባንኩ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የተቀመጡ ህጎችን አክብረው ሲሄዱ ብቻ መሆኑን ወ/ሮ መሰረት አንስተዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የልማት ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ዋቄ ባንኩ ክፍተቶችን ለመሙላት ስትራቴጂ ነድፎ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በመድረኩ በናሙና የተጠቀሱ ብድሮች ወይንም ፕሮጀክቶች ላይ ክፍተቶች እንደነበሩ ቀደም ብለው ያወቁ መሆናቸውን ጠቅሰው ክፍተቱንም ለመድፈን ባንኩ ስትራቴጂ አውጥቶ ሲሰራ እንደነበር ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የደንበኞችን መረጃ በጥልቀት በመመርመርና አሰራራቸውን በዲጂታል በመደገፍ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል ሲል ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያምርላክታል።
ምላሽ ይስጡ