ኢትዮጵያ በእንሰት ምርት የምትታወቅ እና አምራች ሃገር ብትሆነም ከእንሰት ምርት የሚገኘዉን እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚዉለዉን ቃጫ በዉጭ ምንዛሬ ከዉጭ ስታስገባ ቆይታለች፡፡
ለዉሃ መስመር ዝርጋታ እና ለተለያዩ በተፈጥሮ መታሰር(መታሸግ) ለሚፈልጉ ምግብ ነክ ነገሮች በስፋት የሚዉለዉ ቃጫ ኢትዮጵያ ከዉጭ ስታስገባ መቆየቷ ተገልጿል፡፡ ኢትዮጵያ በእንሰትና በሌሎችም ለምግብነት በሚውሉ የእጽዋት አይነቶች የታደለች ብትሆንም የተለያዩ ምርምሮችን በማድረግ ለምግብነትና ለሌሎችም ጉዳዮች ከማዋል አኳያ ከፍተኛ የሆነ ክፍተት እንዳለ የሚገልጹት በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የእንስሳት ተመራማሪ ዶ/ር አዲሱ ፍቃዱ ናቸው፡፡
በሃገራችን የእንሰት ምርት በ5 ክልሎች በስፋት የሚመረት እንደሆነ የሚገልጹት ዶ/ር አዲሱ እንደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተደረገ የ11 ዓመት ጥናት ሃገራችን ከእንሰት ምርት እስካሁን ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳላገኘች አመላክተዋል፡፡
አሁን ላይ 20 ሚሊዮን አካባቢ የሚሆን የህብረተሰብ ክፍል የእንሰት ምርትን ለምግብነት እንደሚጠቀም ገለጹት ዶ/ር አዲሱ ዩኒቨርሲቲው ባደረገው የዳሰሳ ጥናት፤ ለእንሰት ምርት ትኩረት አለመስጠት፤ የአመራረት ዘዴያችን ባህላዊ መሆኑና ለጥራጥሬ ምግቦች ብቻ ከፍተኛ ትኩረት መደረጉ እንደተግዳሮት የሚነሳ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የብሄራዊ እንሰት ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር ሄኖክ ፍቅሬ፤ እንሰትን ለምግብነት፤ ለቃጫነት፤ እንዲሁም ለወረቀት ምርትነት የሚውሉትን የመለየት ስራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡ የእንሰት ተክል በባህሪው እስከ 4 መቶ የሚሆኑ ስሮች ያሉት በመሆኑ ድርቅ ባለባቸው አካባቢዎች በስፋት እንዲተከሉ፣ የአፈር ለምነትም እንዲጠበቅ ለማድረግም እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በምርምር ተቋሙ ውስጥ የእንሰት ቃጫ ላይ በትኩረት በመስራት አሁን ላይ በውጭ ምንዛሬ አማካኝነት ይገባ የነበረውን የቃጫ ምርት እስከ 40 በመቶ መቀነስ እንደተቻለም አመላክተዋል፡፡
በሃገራችን ያለውን የእንሰት ምርት የተለያዩ ዘመናዊ የቴክኖሎጅ ውጤችን በመጠቀም በስፋት ለምግብነትና ሌሎችም ነገሮች ጥቅም ላይ ለማዋል ከግብርና ሚንስቴርና ከተለያዩ የምርምር ተቃማት ጋር በጋራ ለመስራት መታቀዱ ተመላክቷል፡፡
ምላሽ ይስጡ