ጥር 06 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)በአፍሪካ በዓመት 200 ቢሊዮን ዶላር በሙስና እንደሚመዘበር ትራንስፓራንሲ ኢንተርናሽናል ከሰሞኑን ባወጣው መረጃ ገልጿል፡፡
የቀድሞው ዲፕሎማት አምባሳደር ጥሩነህ ዜና የአፍሪካ ሃገራት የአህጉሩን ሃብት በአግባቡ ለሚፈለገው አላማ ቢያውሉት አሁን የሚታየው አይነት ድህነት ላይከሰት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ሙስና በቀላሉ የሚጠፋ አይደለም የሚሉት አምባሳደሩ፤ በአፍሪካ ህብረት ጉባኤም ሆነ በተለያዩ አህጉራዊ መድረኮች በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት ቢደረግም መፍትሄ አልተገኘለትም ብለዋል፡፡
በአህጉሪቱ ስልጣን ለመያዝ እና ሀብት ለመበዝበዝ የሚደረግ ሩጫ እንደሚስተዋል የተናገሩት አምባሳደር ጥሩነህ፤ ከሌሎቹ የአፍሪካ ሃገራት አንጻር በኢትዮጵያ ያለው የሙስና ችግር ከፍተኛ አይደለም ብለዋል፡፡ በተለይ ከኬኒያ ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው የሚሉት አምባሳደሩ፤ ቢሆንም ግን አሁን ላይ በሃገሪቷ ያለውን ብልሹ አሰራር እና ሙስና መቅረፍ ይገባል ብለዋል፡፡
ለዚህም ደግሞ የሚዲያ ነጻነት እና የዴሞክራሲ ስርዓቱን ማሻሻል ይገባል ብለዋል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ በበኩላቸው፤ የአፍሪካ ህብረት የጸረ ሙስና አማካሪ ቦርድ የሚባለው አደረጃጀት በዚሁ ጉዳይ ላይ እንዲሰራ ኃላፊነት ቢሰጠውም፤ የአህጉሩ መንግስታት ራሳቸው በሙስና የሚሳተፉ በመሆኑ አማካሪ ቦርዱ የሚያቀርበውን ሃሳብ አይቀበሉም፤ በዚህም የተነሳ ህብረቱ በሙስና ጉዳይ እስካሁን ምንም ነገር ሊያደርግ አልቻለም ብለዋል፡፡
ቦርዱ በየዓመቱ አጀንዳ ይዞ የሚወያይበት ጉዳይ ቢሆንም ህግ ከማውጣት ያለፈ መፍትሄ የሌለው ነው ያሉት ባለሙያው፤ ከአህጉራዊ ተቋም እና ከመንግስታት ይልቅ ዜጎች፤ ሲቪል ማህበራት እና መገናኛ ብዙሃኑ በጉዳዩ ዙሪያ ቢሰሩ ውጤት ማምጣት ይቻላል ብለዋል፡፡
በአህጉሪቷ የሚታየውን ድህነት ለመቅረፍ ብሎም የአህጉሪቱን ሃብት በስርዓት ለመጠቀም ከመንግስት ውጪ ያሉ የሲቪል ማህበራት እና መገናኛ ብዙሃኑ በትኩረት ሊሰሩበት እንደሚገባ ተመላክቷል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
መናኸሪያ ሬዲዮ 99.1
ሃሳብ፣አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት የሚከተሉትን የስቱዲዮ ስልኮቻችን ይጠቀሙ
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
የቀጥታ ስርጭት 👉 📻 (https://worldradiomap.com/et/play/menaharia) radio 99.1 (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
✅ https://t.me/menaharia_fm
✅ https://x.com/MenahriaFm99_1
ትክክለኛውን የመናኸሪያ ሬዲዮ የዩቱዩብ አድራሻ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
➲ https://youtube.com/@menahriaradio99.1?si=dRLPxb2AKvsMaph-
ምላሽ ይስጡ