በዚህ በያዝነው ዘመናዊው አለም ውስጥ የዲሞክራሲ ስርአት መገለጫ ከሆኑት ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል የፍትህ ስርአት መዘመንና የአሰራር ነጻነት እንደሆነ በብዙዎቹ የዘርፉ ልሂቃን ዘንድ ይነገራል።
መንግስት የትኛውንም አይነት የአስተዳደር ሲስተም ቢጠቀም ህዝብ እንደ ህዝብ ሊያገኘው የሚፈልገው ነገር ፍትህና ሰላም እንዲሁም ዲሞክራሲን ነው ይላሉ ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ መንግስትና የህዝብ አስተዳደር በሚል ጽሁፋቸው። ገብረ ህይወት ባይከዳኝ አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ በሚለው ድርሳናቸው እንደሚሉን፡ አእምሮ የሌለው ሕዝብ ሥራት የለውም፡፡ ሥራትም የሌለው ሕዝብ የደለደለ ኃይል የለውም፡፡ የኃይል ምንጭ ሥርዓት ነው እንጅ የሠራዊት ብዛት አይደለም፡፡
ሥራት ከሌለው ሰፊ መንግስት ይልቅ በሕግ የምትኖር ትንሽ ከተማ ሞያ ትሠራለች። በመሆኑም በዚህ አገላለጽ መሰረት ከጥንትም ለሀገሬው የሚበጀው ህግና ህግ ብቻ መሆኑ ተጠቅሷል። ህጉም ስርአት ተበጅቶለት በአግባቡ ሲፈጸምና ሲተገበር ብቻ እውን እንደሚሆን ብዙዎች ይናገራሉ። የህጎች መፈጸሚያ ቦታ የሆኑት የፍትህ አካላት ታዲያ ህግን ለመተግበር ሁለንተናዊ የአሰራር ነጻነትና ጠንካራ አወቃቀር ያላቸው ተቋማት እንደሚያስፈልጉ ይነገራል። በኛ ሀገር ታሪክ የቱንም ያህል የረጅም ዘመን የህገ መንግስትና የስርአት አወቃቀር ልማድ ቢኖረንም ቅሉ ዛሬም ዘርፉ የሚሰጠው አገልግሎት በብዙዎች ዘንድ የሚተችና ለህዝብ የምሬት ምንጭ ሲሆን ይስተዋላል።
ምንም እንኳን ከለውጡ ማግስት ላለፉት ስድስት አመታት የታዩ የአሰራር ለውጦችና መሻሻሎች ቢኖሩም ዛሬም ግን በርካቶች በተጓተተ አሰራር ምክንያት ፍትህ አጥተው መንገላታታቸውን የሚገልጹ ብዙዎች ናቸው። የዘገየ ፍትህ እንዳልተሰጠ ይቆጠራል እንዲሉ የዘርፉ ልሂቃን ብዙዎች በዚህ በሳይንስና ቴክኖሎጂ በፈጠነ አለም ውስጥ ሳለን በፍትህ መጓተት ምክንያት እየተሰቃየን ነው ሲሉ ይደመጣሉ።
በወንጀል የፍትህ አስተዳደር ሥርዓት ዉስጥ የዜጎች በአፋጣኝ ፍትህ የማግኘት መብት መሰረታዊ የሆነ መብት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ መሰረታዊ የህግ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ አሁን ላይ ዜጎች በፍትህ ስርአቱ ላይ ለሚስተዋለው የተጓተተ አሰራር እንደ ዋነኛ ምክንያት አድርገው ሃሳብ ሲያነሱ ሁለት አጽናፍ ይዘው ሲከራከሩ ይስተዋላል። በአንድ በኩል ዛሬም ድረስ ለሚስተዋለው የፍትህ ስርአቱ መጓተት ዋነኛ ምክንያት የፍትህ ተቋማቱ አለመጠናከር ነው የሚሉ ሲኖሩ የለም እሱ አይደለም በማለት ደግሞ በሌላ በኩል ቆመው ሃሳብ የሚያነሱ ወገኖች ደግሞ ሲናገሩ ለፍትህ ስርአቱ እጅግ የተጓተተ አሰራር ዋነኛ ምክንያት የአስፈጻሚ አካላቱ ድክመት መሆኑን ሲጠቅሱ ይስተዋላል። ክርክሩ እነሆ ከትላንት እስከዛሬ እንደቀጠለ ነው።
ለተጓተተው የፍትህ ስርአቱ ሂደት ምክንያት የአስፈጻሚዎች ድክመት መሆኑን የሚናገሩት ወገኖች ሃሳብ ሲያነሱ ፦ እንደ ሀገር የህግ ማእቀፍና የአወቃቀር ችግር የለብንም ሲሉ ይጠቅሳሉ። በሀገራችን የሕግ ማዕቀፍ መሰረት አፋጣኝ ፍትሕ የማግኘት መብት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት በአንቀፅ 20 (1) ስር የተከሰሱ ሰዎች ክስ ከቀረበባቸው በኋላ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ በመደበኛ ፍርድ ቤት ለሕዝብ ግልፅ በሆነ ችሎት የመስማት መብት ያላቸው መሆኑ ተመላክቷል። በመሆኑም ከዚህ የሕገ መንግሥት ድንጋጌ እንደምንረዳው የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት መረጋገጥ ያለበት እንደየጉዳዩ ሁኔታ ግልጽ በሆነ ችሎት ሲሆን፤ ይህ ሲባል ከተከሳሹ በተጨማሪ ማህበረሰቡም ስለ ጉዳዩ ሂደት በቂ ግንዛቤ እንዲኖረውና ፍትህ ሲሰጥ ለመታዘብ ወይም ለማየት እድል ይሰጠዋል ሲሉ ከፈጻሚዎቹና ከአስፈጻሚዎቹ እንጂ ምንም አይነት የህግ ማእቀፍ ክፍተት እንደሌለ የሚናገሩት ወገኖች ያስረዳሉ። አክለውም ከጊዜ ቀጠሮ ጋር በተገናኘ፣ ከምርመራ ጊዜና ሪፖርት አደራረግ ጋርም በተገናኘ እንዲሁም ምርመራ ከተጠናቀቀ በኋላም በአቃቤ ህግ በኩልም ሆነ በፍርድ ቤት በኩል በጉዳዩ ላይ በጊዜ ውሳኔ መስጠት እንደሚያስፈልግና መሰል ድንጋጌዎችም በህጉ ዝርዝር ውስጥ ይገኛሉ ይላሉ። ይሁን እንጂ ህጉ ይህን መሰል አጋዥ ማእቀፎችን ይዞ ቢቀመጥም ፈጻሚና አስፈጻሚ አካላት በሃላፊነትና በህጉ መሰረት ባለመስራታቸው ምክንያት ደንበኞች ዘወትር እየተጉላሉ ቀጥለዋል ሲሉ በዚህ ወገን ያሉት ለችግሩ ምንጭ ፈጻሚም አስፈጻሚም አካላት ናቸው ይላሉ።
ለተጓተተው የፍትህ ስርአቱ ሂደት ምክንያት የአስፈጻሚዎች ድክመት ሳይሆን የፍትህ ስርአቱን የሚመሩ ተቋማቱ በራሳቸው የተጠናከሩ አለመሆን ነው የሚሉት ወገኖች ደግሞ ሃሳብ ሲያነሱ፦ የፍትህ ተቋማት እንደ ሀገር በጥቅሉ ሲታይ የተደራጁና በአሰራርም ደግሞ ገለልተኛና ነጻ አይደሉም ሲሉ ይናገራሉ። የኢትዮጵያ የፍትሕ ተቋማት ቋንቋ፣ አደረጃጀትና መፈክር ከሕገ መንግሥት ይልቅ ለፓርቲ አቋም ይበልጥ የተገዛ መሆኑን በዘመናት ታሪካችን ውስጥ ከኋላ እስከ ጀምረን እስካሁን ድረስ መመልከት እንችላለን ሲሉ የዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታና የሽግግር ፖለቲካ ተግዳሮቶች በኢትዮጵያ በሚል ጥናታዊ ጽሁፋቸው አቶ በቃሉ ዋቺሶ ይናገራሉ። የፍትህ አካላት ፖለቲካዊ ቋንቋንና የመንግስትን የየእለት የፕሮፖጋንዳ ቃላት ሲጠቀሙ ሁሉ ይሰማሉ በማለት የኢህአዴግ የቁልቁለት ጉዞ በተሰኘው መጽሃፋቸው አቶ ብርሃነ ጽጋብ ይናገራሉ። በሕገ መንግሥቱ መሰረት የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው ቢባልም ይላሉ በዚህ ወገን የቆሙት ደግሞ ሲቀጥሉ፦ ከላይ እስከታች የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት አለበት ይህም ማለት ከፍትህ ሚኒስቴር ውጭ ያሉ የፖለቲካ ባለስልጣናት ጣልቃገብነት ይታያል ይላሉ። አንዳንድ ግዜ ፍርድ ቤት ነጻ ያለውን አካል ፖሊስ አለቅም የሚልበት አጋጣሚም ይታያል በማለት እነዚህን የመሳሰሉት አካሄዶች ደግሞ ጠንካራ ባልሆኑ የፍትህ ተቋማቶች ውስጥ የሚስተዋሉ አሰራሮች ናቸው ሲሉ ብርካቶች ይናገራሉ። ለፍትህ መጓተት ዋነኛ ምክንያቱ ተቋማዊ አደረጃጀቱ ነው በማለት የተቋማት ጠንካራ ሆኖ አለመገኘትን እንደ ምክንያት የሚያነሱት ወገኖች ሃሳባቸውን ሲቀጥሉ፦ ዓቃቤ ሕግ በአግባቡ ሥራውን እንዳይሰራ፣ ፖሊስ የሚፈለግበትን ኃላፊነት እንዳይወጣ፣ ማረሚያ ቤቶች በሕጉ መሠረት ታራሚዎችን እንዳያስተናግዱና ፍርድ ቤቶች የጉልበተኞች መፈንጫ እንዲሆኑ የሚያደርገውና ያደረገው ተቋማዊ አቋሙ ጠንካራ ባለመሆኑ ነው ሲሉ ይናገራሉ። ለዚህም ደግሞ ዋነኛ ምክንያቱ ትክክለኛ የዲሞክራሲ አለመተግበር ነው ሲሉ በዚህ ወገን ያሉት ያስረዳሉ። በሕዝብና በመንግሥት መካከል መተማመን እንዲጠፋ የሚያደርገው የፍትህ መጓደል ነው የሚሉት በዚህ በኩል ያሉቱ ተቋማቱ ዲሞክራሲያን ያላስተጋቡና እያስተጋቡም ያልሆኑ በከፍተኛ ፖለቲካዊ ጣልቃገብነት ውስጥ የሚዋዥቁ ሆነው ስለሚስተዋል እንደ ሀገር የፍትህ ተቋማት የዲሞክራሲያዊ ስርአት ማሳያ ለመሆን የበቁ አይደሉም ይላሉ የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ጌትዬ ትርፌ ሲናገሩ። የፍትሕ ሥርዓቱ ከሚተችባቸው በርካታ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የገዢ ፓርቲዎችን የልብ ትርታ እያዳመጠ መንቀሳቀሱ ነው ሲሉም ጸሃፊው አቶ ብርሃነ ጽጋብ ይናገራሉ። የፍትሕ ሥርዓቱ አካላት ሥራቸውን በነፃነት ማከናወን ሲገባቸው፣ አላስፈላጊ ሥምሪት ውስጥ ገብተው ፍትሕ እንዲደረመስ ማድረጋቸውም እሙን ነው የሚሉት በርካቶች በዚህም ምክንያት ጉቦና ምልጃ ውስጥ ሲገቡም ይስተዋላሉ ይላሉ። ከመጀመርያው ምርመራ ጀምሮ እስከ መጨረሻው የፍርድ ውሳኔ ድረስ ሕዝብን የሚያማርሩ አስከፊ ድርጊቶች እንዲበዙ የተቋማት ደካማ ሆኖ መገኘትና የዲሞክራሲያዊ ሃሳብና መንፈስ በተቋማቱ ላይ አለመስረጽ ሁነኛ አስተዋጾ አድርጓል ይላሉ።
የለም የለም ለተጓተተው የፍትህ ስርአቱ ሂደት ምክንያት የአስፈጻሚዎች ድክመት እንጂ የተቋማቱ ጉዳይ አይደለም ሲሉ የሚከራከሩት ደግሞ መልሰው ሲናገሩ፦ በአንድ በኩል የሕብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅና ለማስጠበቅ የወንጀል ድርጊት ፈፃሚዎችን ለፍርድ አቅርቦ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ ሲሆን በሌላ በኩል ቅጣቱ የሚፈፀመው በአጥፊ ሰዎች ላይ ብቻ አንደሚሆንና እነዚህም ቢሆኑ ለጥፋታቸው ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት እንዲያገኙ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ነው፡፡ መንግሥት እነዚህን ሁለት ተፋላሚ ፍላጎቶችን አጣጥሞ የወንጀል ሕጉን ትርጉም ባለው መልኩ ለማስፈፀም የሚያስችል ውጤታማ፣ ቀልጣፋ፣ ሚዛናዊ፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ተደራሽ እና ከፍተኛ የሕዝብ አመኔታ ያለው አሠራር በመዘርጋት በአፍርድ ቤቶች በኩል የፈጻሚነት ስልጣን ቢሰጥም በዚያ ፈጻሚም አስፈጻሚም አካላት በሚሰሩት ዘርፈ ብዙ ደካማ አሰራሮች ምክንያት የህዝብ እሮሮ ሊቀረፍ አልቻለም ሲሉ ‘’ዳኞች፣ ዐቃቤ ሕጎች፣ ጠበቆች እና ፖሊሶች ሊዘነጓቸው የማይገቡ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ መርህዎች’’ በሚል መጣጥፋቸው አቶ ሊቁ ወርቁ የተባሉ የህግ ባለሙያ ያስረዳሉ።
ለእያንዳንዱ የየእለት የፍርድ ቤት ጉዳዮቻቸው ደንበኞች ከሚያነሱት የዘወትር ቅሬታ መካከል ዋነኛው የተጓተተ ውሳኔ ነው የሚሉት በዚህ ወገን ያሉት ሲቀጥሉ፦ የዳኞች መቀያየር፣ በተቀመጠው የህግ ማእቀፍ መሰረት አለመወሰን፣ ለጉዳዮች ቸልተኛ መሆን ሲሆኑ ከፍ ሲልም የዳኞች የእውቀት ክፍተት መሆኑን ያነሳሉ። በአስተዳደራዊ አሰራሮች የዘመኑን የቴክኖሎጂ ሲስተም መርህና አካሄድ ቢስተዋልም በተግባር ከሚወሰኑ የፍርድ ውሳኔዎችና አሰጣጥፕች ጋር በተገናኘ ግን ፈጣን ቀልጣፋና ብቁ ጥራት ያለው አይደለም በማለት ለዚህም ምክንያቱን ደግሞ ከፍትህ ተቋማት ጥቅል ክፍተት ይልቅ የፈጻሚና የአስፈጻሚ አካላትን ድክመት እንደ ዋነኛ ነጥብ የሚያነሱ ብዙዎች ናቸው።
ለዘርፉ የአገልግሎትም ሆነ የህግ ማእቀፍ ችግር ዋነኛ መሰረቱ ከታች ባሉ የፍትህ አካላት ዘንድ ብቻ መታየት የለበትም በማለት ጉዳዩ እንደ ሀገር ተቋማዊ ነው ሲሉ የፍትህ ተቋማትን አለመጠናከር እንደምክንያት የሚናገሩት ወገኖች መልሰው መከራከሪያ ሃሳብ ሲያነሱ ደግሞ፦ ከታች ባሉት ፈጻሚና አስፈጻሚ አካላት ላይ ተጽእኖ የሚያሳድረው የተቋማቱ በቅጡ አለመደራጀት ነው ይላሉ። ለዚህም ደግሞ እንደ ሀገር ነጻና ገለልተኛ የፍትህ አካላትን መመስረት አለመቻሉ ነው በሚል ይናገራሉ። ዘርፉ የህዝብ አመኔታ እንዳይኖረው ከሚያደርገው አንዱ መንገድ ገለልተኛና ነጻ ዲሞክራሲያዊ አሰራር ባለመከተሉ ነው ሲሉ አዳፍኔ በሚል መጽሃፋቸው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ጠቅሰው እንደነበር ይጠቀሳል። ተቋማዊውን ድክመት የሚያነሱት ወገኖች አክለውም፦ ፍርድ ቤቶች በነፃነትና በገለልተኝነት እንዳይሠሩ ሲደረግ ይዳከማሉ፣ የዚህ ዳፋ ዳኞችን በሕጉና በህሊናቸው እየተመሩ መፍረድ እንዳይችሉም ያደርጋቸዋል ይላሉ። እንዲሁም በተቋማቱ ከፖለቲካ የተገለሉ አለመሆን የዳኞች አሿሿም ከምልመላው ጀምሮ ከብቃት ይልቅ የፖለቲካ ወገንተኝነታቸው ብቻ እንዲታይ ያደርገዋል በዚህም አካሄድ ፍትህና ፍትሃዊ ስርአት ሊገነባ አይችልም ይላሉ።
ዘርፉ ዲሞክራሲ የምይተገበርበትና ከፖለቲካ ነጻ ያልሆነ በመሆኑም ምክንያት ነው ለተለያዩ ሀገራዊ ችግሮቻችን መፍቻ መፍትሄ የሽግግር ፍትህ በሚል ሌላ ጊዜያዊ አደረጃጀት መስርተን የነበረው ሲሉ የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ጌትዬ ትርፌም ካሁን ቀደም ደጋግመው ሲያነሱት ነበር።
በሰለጠኑት ሀገራት የዲሞክራሲያዊ ስርአት ዋነኛ መታያ መንጸባረቂያ ስፍራዎች የፍትህ አካላት ናቸው የሚሉት የህግ ባለሙያውና ጦማሪው አቶ ሊቁ ወርቁ ሲናገሩ በኛ ሀገር ደግሞ የዲሞክራሲያዊ ሂደት መታያ የሆኑትን በቃል የሚነዙ የፖለቲካ ቋንቋዎችን በፍትህ አካላት ውስጥም ከመስማት የዘለለ ዜጎች በዘርፉ እውነተኛ ፍትህ እንብዛም ሲያገኙ አይስተዋልም ይላሉ። ዛሬም ድረስ ማረሚያ ቤቶች በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሳይቀር በየጊዜው ሪፖርት የሚቀርብባቸው ስፍራዎች ናቸው የሚሉት ጸሃፊው በስፍራው ይፈጸማሉ የሚባሉት ህገ ወጥ ጉዳዮች የፍትህ አካላትን የነፃና የገለልተኝነት ጉዳይ ገደል የሚከቱ ናቸው ብለዋል፡፡
ጉዳዩን እንደ ተቋም ብቻ በመውሰድ ወይም በጥቅሉ በፍትህ ዘርፉ በማመካኘት መፍትሄ አይገኝም በማለት አሁንም ለፍትህ ስርአቱ መጓተትና ሁለንተናዊ ችግር ምክንያቱ ፈጻሚና አስፈጻሚ አካላት ናቸው ሲሉ የሚከራከሩት ወገኖች ደግሞ ሃሳባቸውን አንስተው ሲከራከሩ ፦ በታችኛው ዘርፍ ያሉ የፍትህ አካላት መጠየቅ አለባቸው ይላሉ። ዳኞች ነፃነታቸውን በተጠያቂነት መርህ መስራት አለባቸው፣ ዓቃቢያነ ሕግ ለጥፋታቸው መጠየቅ አለባቸው፣ ፖሊስና ማረሚያ ቤቶች የሕግ ክፍተት ሳይኖር በአፈጻጸም ክፍተት ብቻ ለሚያደርሱት እንግልት ተጠያቂ መደረግ መቻል አለባቸው ይላሉ። በዘርፉ ደንበኞች ፍትህን በገንዘብ ለማስፈጸም ሲሞክርና መሰል የሙስና ድርጊቶችም ሲከናወኑ አለማስተካከል የታችኛው የአስፈጻሚ አካል ችግር እንጂ የጥቅል የፍትህ ተቋማቱ ችግር አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ። በመሆኑም ሕገወጥነት የበላይነቱን የሚይዘው በሕግ የበላይነት ላይ ከሆነ ህጉን የሚፈጽሙት ፈጻሚ አካላት ፍርድ ቤቶችም ሆኑ በዚያ ውስጥ በፍርድ ሂደት ውስጥ የሚመላለሱት ባለሙያዎች በሙሉ ችግሩን ለመቅረፍ ቀጥተኛ ሃላፊነት አለባቸው ይላሉ።
ውድ አድማጮቻችን ለተጓተተው የፍትህ ስርአቱ ሂደት ምክንያት የተቋማቱ አለመጠናከር ወይስ የአስፈጻሚ አካላት ክፍተት በሚል ርእሰ ጉዳይ የዛሬው የግራና ቀኝ የሃሳብ መሰናዶ የተከታተላችሁትን ይመስላል። እናንተስ ምን ትላላችሁ? በያላችሁበት ተወያዩበት። ሳምንት በሌላ የግራና ቀኝ የሃሳብ መሰናዶ እስክንገናኝ ቸር እንሰንብት።
ምላሽ ይስጡ