ኅዳር 16 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በዚህ አመት እንደ ሀገር ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ የቡና ምርት ለመሰብሰብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡
ባለፉት አመታት የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች በበጀት ዓመቱ ከባለፉት ጊዜያት የተሻል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳሬክትር አቶ ታጋይ ኑሩ ተናግረዋል፡፡
በሁሉም ቡና አብቃይ ክልሎች ያለው የምርት ሁኔታ ዘንድሮ ከፍ ያለ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ባለፈው አመት ወደ ዉጭ ከተላከው 298 ሺህ 500 ቶን ቡና 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን በማስታወስ፤ በዘንድሮ አመት ወደ 450 ሺህ ቶን ቡና ወደ ዉጭ በመላክ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የቡናና ፍራፍሬ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሀመድሳኒ አሚን 70 በመቶ ያህሉ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ቡና ከክልሉ የሚሰበሰብ እንደመሆኑ መጠን ጥራት እና ምርታማነቱን ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ አሁን ላይ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የቡና ምርትን የመሰብሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑን በመግለጽ፤ በዓመቱ ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቶን በላይ የቡና ምርት ለመሰብሰብ በዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ የሲዳማ ክልልም በበጀት ዓመቱ ከቡና ምርት የተሻለ ገቢ ለማግኘት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የክልሉ የቡና፤ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ቃሬ በክልሉ በአጠቃላይ ወደ 159 ሺህ ቶን ቡና እንደሚመረትና 40 ሺህ ቶን ያህሉ ለማዕከላዊ ገቢያ እንደሚቀርብ ገልጸዋል፡፡
እስካሁን ባለው ሂደት 51 በመቶ ያህል ምርት መሰብሰብ መቻሉንም ነው ያስታወቁት፡፡
ቡና በአፍሪካ ነፃ ገበያ የሚቀርብ ተቀዳሚው ምርት እንደሚሆን በቅርቡ መገለጹ ይታወቃል፡፡ በመሆኑን በዚህ ዓመት ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለገበያ ለማቅረብ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
መናኸሪያ ሬዲዮ 99.1
ሃሳብ፣አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት የሚከተሉትን የስቱዲዮ ስልኮቻችን ይጠቀሙ
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
የቀጥታ ስርጭት 👉 📻 (https://worldradiomap.com/et/play/menaharia) radio 99.1 (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
✅ Telegram (https://t.me/menaharia_fm)
ትክክለኛውን የመናኸሪያ ሬዲዮ የዩቱዩብ አድራሻ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
➲ Youtube (https://www.youtube.com/channel/UC8uROsU69D8Ob65XapeHvIw)
ምላሽ ይስጡ