ኅዳር 11 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን በእጅጉ እየፈተኑ ከሚገኙ ጉዳዮች መካከል አንዱ የትራንስፖርት እጥረት መሆኑ ይታወቃል፡፡ መንግስት የትራንስፖርት እጥረቱን ለመፍታት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ በተደጋጋሚ የሚገልጹት ጉዳይ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አዉቶቡስ ድርጅት በከተማዋ የሚስተዋለውን የትራንስፖርት እጥረት ለመፍታት የአገልግሎት አሰጣጡን እስከ ምሽት 4 ሰዓት እንዲራዘም ማድረጉን የድርጅቱ የኢንተለጀንስ ትራንስፓርት ሲስተምና ኦፕሬሽን አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰብስባቸዉ መንግስቴ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ 7/24 የሚል እቀድ መያዙን የተናገሩት አቶ ሰብስባቸው ለጊዜው በምሽት የሚያጋጥመውን የትራንስፖርት እጥረት ለመፍታት ጎሮ እና መገናኛ ሙሉ በሙሉ እስከ ምሽት 4 ሰዓት አገልግሎቱ እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡
በትላንትናው ዕለትም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 4ተኛ ዓመት አንደኛ መደበኛ ስብሰባ የሩብ አመት ዕቅድ አፈጻጸም ላይ የከተማ አውቶቡስ ትራንስፓርት አገልግሎት ሰዓት ስለመራዘሙ ይፋ የተደረገ ሲሆን ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ የሸገርና አንበሳ አዉቶብስ ተብለዉ በተናጠል የነበሩት ተቋማት የአዲስ አበባ ከተማ አዉቶብስ ድርጅት በሚል በአንድ ላይ መቀናጀታቸዉ ይታወሳል፡፡
ምላሽ ይስጡ