ኅዳር 06 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) የስኳር መድሃኒት እጥረት እንደሌለ የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ቢገልጽም በመድሃኒት መሸጫ መደብሮች የኢንሱሊን እጥረት መኖሩን የመድሃኒት መሸጫ መደብር ባለቤት እና ባለሙያዎች ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቀዋል።
እንደ ኢንሱሊን ያሉ መሰረታዊ የስኳር መድሃኒቶች እጥረት መኖር እንደማይገባው በመግለጽ አሁን ላይ እጥረት ከሚስተዋልባቸው መድሃኒቶች አንዱ መሆኑን የከነማ መድሃኒት ቤት ቁጥር አስራ አራት ተጠባባቂ ሃላፊ አቶ ታጠቅ ታደሰ ለጣቢያችን ገልጸዋል።
በብዛት ከሚሸጡ የስኳር መድሃኒት አይነቶች ዋነኛው የሆነው ኢንሱሊን ከተፈላጊነቱ አንጻር ቶሎ እንደሚያልቅ ሃላፊው አስረድተዋል።
የመድሃኒት መሸጫ መደብሮቹ ምርቱን ሲጠይቁ የተፈለጉት መድሃኒቶች በቶሎ እንደማይቀርብላቸው የገለጹት ኃላፊው፤ ይህ አይነቱ አሰራር ሊቀረፍ ይገባል ብለዋል፡፡
በመርፌ የሚወሰዱት መድሃኒቶች ለውስን ሰአት በፍሪጅ የሚቀመጡ በመሆናቸው በተፈለገው ሰዓት ሁሉ በቂ አቅርቦት ሊኖርና በፍጥነትም አገልግሎት ላይ መዋል እንዳለበት ነው ሃላፊው የተናገሩት።
እንደ ግል የመድሃኒት መሸጫ መደብር ከኢትዮጵያ መድሐኒት አቅራቢ አገልግሎቱ የሚቀርብላቸው ምርት ባይኖርም፤ በጥቅሉ በመሸጫ መደብሩ የኢንሱሊን እጥረት መኖሩን የገለጹት የኢል-ጊቦር መድሃኒት መሸጫ መደብር ፋርማሲስት ወ/ሪት ሃናኒ አብርሃም ናቸው፡፡ መድሐኒቱ ከገበያ መጥፋቱንም ነው የተናገሩት፡፡
የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው አሁን ላይ ኢንሱሊንን ጨምሮ ሁሉም አይነት የስኳር መድሃኒት በበቂ ሁኔታ መኖሩን ለጣቢያችን ገልጸዋል።
መንግስት የስኳር መድሃኒትን በከነማ መድሃኒት ቤቶች በበቂ ሁኔታ አቅርቧል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ነገር ግን የግል መድሃኒት አቅራቢዎችም ሆኑ መሸጫ መደብሮች በውድ ዋጋ ለህብረተሰቡ እንዳይቀርቡ ሲባል እንደማይሰራጭላቸው አስታውቀዋል።
አሁን ላይ አንዳንድ የግል መደብሮች የአገልግሎት አቅራቢውን አርማ በመጠቀም በውድ ዋጋ የሚያቀርቡ እንዳሉ እና ይህን ባደረጉት ላይ እርምጃ እንደተወሰደባቸውም ዶክተር አብዱልቃድር ገልጸዋል።
በመዲናዋ ያሉ አንዳንድ የመድሐኒት መሸጫ መደብሮች የኢንሱሊን እጥረት እንዳለ ቢገልጹም፤ የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት በበኩሉ በቂ አቅርቦት እንዳለ አስታውቋል።
ምላሽ ይስጡ