አውሮፕላኖች ያለ መስኮት?

የአየር ጉዞን የሚቀይር አዲስ ጽንሰ-ሀሳብ

መስከረም 06 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ) የአውሮፓ የዲዛይን ድርጅቶች አየር መንገዱን ሙሉ ለሙሉ ሊቀይር የሚችል አዲስ የአውሮፕላን ንድፍ ይፋ አድርገዋል። እነዚህ አውሮፕላኖች ባህላዊ መስኮቶች አይኖራቸውም፤ በምትኩ እጅግ በጣም ቀጭንና ተጣጣፊ የሆኑ የኦኤልኢዲ (OLED) ስክሪኖች በአውሮፕላኑ ግድግዳና ጣሪያ ላይ ይጫናሉ።

ይህ አብዮታዊ ንድፍ፣ ከአውሮፕላኑ ውጭ የተገጠሙ ካሜራዎች የሚያነሷቸውን ምስሎች በእውነተኛ ሰዓት ለስክሪኖቹ በማስተላለፍ፣ ተሳፋሪዎች ሰማዩንና የመሬት ገጽታን በቀጥታ የሚያዩበትን ምናባዊ እይታ ይፈጥራል። ይህ ዲዛይን የአውሮፕላኑን ግድግዳዎች “ግልጽ” የሚያደርግ በማስመሰል፣ ተሳፋሪዎች ሙሉ ፓኖራሚክ እይታ እንዲኖራቸው ያስችላል ተብሏል።

ዋና ጥቅሞች ተብለው ከተገለጹት መካከል ክብደት መቀነስ ይረዳል የተባለ ሲሆን መስኮቶችን ማስወገድ የአውሮፕላኑን መዋቅራዊ ክብደት በእጅጉ ይቀንሳል። ይህ ደግሞ የነዳጅ ፍጆታን በመቀነስ የካርበን ልቀትን ያሳንሳል ተብሏል።

ስክሪኖቹ ለመዝናኛ፣ ለብርሃን ማስተካከያ ሊያገለግሉ ይችላሉም የተባለ ሲሆን ቴክኒኮን ዲዛይን (Technicon Design) የተሰኘው ኩባንያ የፈጠረው “አይክሲዮን” (IXION) የተሰኘው ጽንሰ-ሀሳብ፣ ለውስጣዊ ስርዓቶቹ ኃይል ለመስጠት የፀሐይ ኃይል ሰሌዳዎችን ይጠቀማል ተብሏል ።

ምንም እንኳን የፅንሰ-ሀሳቡ ጠቀሜታዎች ከፍተኛ ቢሆኑም፣ ለትግበራው እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮች አሉ ተብሏል።

ከእነዚህም መካከል የአውሮፕላኑ ሁኔታ ከስክሪኖቹ እይታ ጋር ላይጣጣም ስለሚችል፣ አንዳንድ ተሳፋሪዎች የእንቅስቃሴ ህመም ሊሰማቸው ይችላል ተብሏል፡፡

በተፈጥሮ ብርሃንና እውነተኛ መስኮቶች እጦት ምክንያት የክላስትሮፎቢያ ስሜት ሊፈጠር ስለሚችል የስነ ልቦና ምቾት ላይ ችግር ሊፈጥርም ይችላል ነው የተባለው፡፡

ፅንሰ-ሀሳቡ ጥብቅ የሆኑ የአየር መንገዶች የደህንነት ደንቦችን ለማሟላት ተጨማሪ ጥናትና ሙከራ ያስፈልገዋል።

የፅንሰ-ሀሳቡ ቀጣይነት ባይረጋገጥም፣ ይህ ፈጠራ የወደፊቱ የአየር ጉዞ ምን ያህል አስደሳችና መሳጭ ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ እንደሚሰጥ ተመላክቷል።

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm

__

ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞

👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉  https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)