ሕዳር 11 ቀን 2019(መናኸሪያ ሬዲዮ)በኢትዮጵያ የአርብቶ አደርነትን ሕይወትና ባህል ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ወጣት አርብቶ አደሮችን በዘርፉ እንዲቀጥሉ ማበረታታትና በየዓመቱ የሚከበረውን የአርብቶ አደሮች ቀን በተገቢው መንገድ ማክበር ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች ፎረም (ፓስቶራሊስት ፎረም ኢትዮጵያ(PFE)) ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የ2026 ዓለም አቀፉን የግጦሽ መሬቶችና የአርብቶ አደሮች ዓመት (UNIYRP 2026) እንዲሁም በኢትዮጵያ ያለውን የአርብቶ አደርነት ሁኔታ አስመልክቶ ኅዳር 10 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ ራስ ሆቴል ለጋዜጠኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ አውደ ጥናት አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ በአርብቶ አደርነት ዘርፍ ዙሪያ ያሉ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎች ሲዳሰሱ፣ በተለይም አዲሱ ትውልድ እና ወጣት አርብቶ አደሮች የወላጆቻቸውን ሙያና የአኗኗር ዘይቤ ሳይለቁ በዘመናዊ መንገድ እንዴት አርብቶ አደር ሆነው እንዲቀጥሉ ማድረግ ይቻላል የሚለው ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶበታል። ከዚህም ባሻገር የአርብቶ አደሮችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ የሚያጎላው የአርብቶ አደሮች ቀን ለምን በሰፊውና በተጠናከረ መልኩ አይከበርም የሚለው ጥያቄ ተነስቶ ውይይት ተደርጎበታል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የግጦሽ መሬቶችና አርብቶ አደሮች ለምግብ ዋስትና፣ ለብዝኃ ሕይወት ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ያላቸውን ጉልህ ድርሻ በመገንዘብ የአውሮፓውያኑን 2026 ዓመት «ዓለም አቀፍ የግጦሽ መሬቶችና የአርብቶ አደሮች ዓመት» ብሎ መሰየሙ ይታወሳል።

በዓለም ዙሪያ ከ102 በላይ ሀገራት እና ከ439 በላይ ተቋማት በሚደግፉትና ባለፈው ነሐሴ ወር በሞንጎሊያ ኡላንባታር በይፋ በተጀመረው በዚህ ዓለም አቀፍ ንቅናቄ ውስጥ፣ መገናኛ ብዙኃን የአርብቶ አደሮችን ድምፅ በማሰማትና ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ግንባር ቀደም ሚናቸውን እንዲወጡ የፎረሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተዘራ ጌታሁን ጥሪ አቅርበዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ