ጥቅምት 30 ቀን 2019(መናኸሪያ ሬዲዮ) በእግር ጫማዎ ላይ ትንንሽ ጉድጓዶች ወይም ነጠብጣቦች እየተፈጠሩብዎት ነው? የእግርዎ ሽታስ ከመጠን በላይ ከባድ ሆኗል? ይህ ችግር ቀላል የንጽህና ጉድለት ብቻ ይመስልዎታል? የቆዳ ህክምና ባለሙያዎች እንደሚያብራሩት፣ «ፒቲድ ኬራቶላይሲስ» (Pitted Keratolysis) በመባል የሚታወቀው ይህ የባክቴሪያ ኢንፌክሽን በተለይ በእግር የታችኛው ክፍል፣ ተረከዝ እና ክብደት በሚያርፍባቸው የእግር ክፍሎች ላይ በስፋት የሚከሰት ችግር ነው።
ለዚህ ችግር ለረጅም ጊዜ የተዘጉ ጫማዎችን መጠቀም፣ እግር በብዛት ላብ ማላብ፣ እርጥብ ካልሲና ጫማ ለረጅም ሰዓታት ማደረግ፣ እንዲሁም ሞቃታማና እርጥበት ያለው አየር ለባክቴሪያው መፈጠር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ። በበሽታው ሲጠቃ በእግር ጫማ ላይ ትንንሽ ጉድጓዶች መፈጠር፣ ከመጠን በላይ ላብ መብዛት፣ የመጥፎ ሽታ መጨመር፣ እና አንዳንድ ጊዜ ማሳከክና ህመም ሊኖሩ ይችላሉ።
ይህ በሽታ በተገቢው ሕክምና በቀላሉ ሊድን የሚችል ሲሆን፤ እንደ ክሊንዳማይሲን (Clindamycin) ወይም ኤርትሮማይሲን (Erythromycin) ያሉ የቆዳ ላይ አንቲባዮቲኮችን በሐኪም ትዕዛዝ ለ2 እስከ 4 ሳምንታት በመጠቀም መቆጣጠር ይቻላል።
እንዲሁም እግርን በየቀኑ በሳሙና መታጠብ፣ ከታጠበ በኋላ በጣቶች መካከል በደንብ ማድረቅ፣ ካልሲን በየቀኑ መቀየር እና አየር የሚያስገቡ ጫማዎችን መምረጥ በሽታውን ለመከላከል ቁልፍ መፍትሄዎች ናቸው ተብሏል።
የእግር መጥፎ ሽታ ሁልጊዜ የንጽህና ጉድለት ሳይሆን የዚህ አይነት የቆዳ በሽታ ምልክት ሊሆን ስለሚችል፣ ምልክቶቹ ካሉዎት የቆዳ ህክምና ባለሙያ ማማከር ይመከራል።
በጌታሁን አስናቀ
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ