ነሐሴ 22 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የቡርኪና ፋሶ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ትራኦሬ የሀገር ፍቅር ስልጠና የሰለጠኑ 65,000 ወጣቶች በምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ በመገኘት የሀገራቸውን ሉአላዊነት እና አንድነት ለማስጠበቅ ትጉ ሆነው እንዲሰሩ ጥሪ አቀረቡ። የትራኦሬ አስተዳደር 2025 ግዴታ የሆነውን የሀገር ፍቅር ማሰልጠኛ ፕሮግራም ያስጀመረ ሲሆን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት ለአንድ ወር የሚቆይ ስልጠና እንዲወስዱ ይደረጋል። ስልጠናው በዜግነት እሴቶች፣ በሀገራዊ አንድነት፣ በዲሲፕሊን እና ታሪክ ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ለዩኒቨርሲቲ ምዝገባ የሚያስፈልገው የምስክር ወረቀት የሚሰጠው ይህን ስልጠና ላጠናቀቁ ተማሪዎች ብቻ ነው። የቡርኪና ፋሶው መሪ ወጣቶቹ አለምን እና ጂኦፖለቲክስን ለመረዳት በሚጥሩበት ወቅት የትህትና እና የሀገር ፍቅር እሴቶችን እንዲላበሱ አሳስበዋል። ከፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት በወጣው መግለጫ መሠረት፣ ፕሬዝዳንቱ በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር “መሃይም የሆነ ሰው ለትግላችን እና ለለውጣችን አደገኛ ነው” ብለዋል። ቀጥለውም ለወጣቶቹ ባስተላለፉት መልዕክት “ምንም አይነት ሁኔታ ቢፈጠር እራሳችሁን በማብቃት ልቃችሁ መገኘት አለባችሁ፤ አጭር መንገድ ወይም ቀላል መንገድን ከመከተል ተቆጠቡ፣ ምክንያቱም ያ መንገድ ወደ ክህደት ያመራል” ሲሉ አሳስበዋል። ባለስልጣናቱ እንደገለጹት ይህ የሁለተኛው ዙር የተማሪዎች ምረቃ ሲሆን፣ የፕሮግራሙ ዋና አላማ የማህበራዊ ትስስርን ማጠናከር እና ለሀገራቸው ቁርጠኛ የሆኑ ዜጎችን መፍጠር እንደሆነ ገልጸዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ