ሰኔ 11 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) ኮሚሽኑ ከ1 ሺህ 200 በላይ ወረዳዎች ላይ አጀንዳዎችን መሰብሰቡን በመጥቀስ፣ በአማራ ክልል ካሉት ከ4 መቶ በላይ ወረዳዎች ውስጥ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት በ4 ወረዳዎች ላይ ግን ውይይት አለመካሄዱን ኮሚሽነር ዶ/ር አምባዬ ኦጋቶ ገልፀዋል፡፡
በትግራይም በተመሳሳይ ከ22 ጊዜ በላይ ውይይቶች ከተካሄዱ በኋላ አመቺ ሁኔታ ባለመኖሩ፣ ውይይቱን በአዲስ አበባ ከክልሉ ተወካዮች ጋር ማካሄዱን አስረድተዋል፡፡
በመጨረሻው የምክክር ወቅት ተሳታፊዎች አንድ ሳምንት ቀደም ብለው አዲስ አበባ እንደሚገቡና ይህም ተሳታፊዎች በምክክሩ ሂደት ላይ እንዲተማመኑና እንዲግባቡ የሚያስችል መሆኑን ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ ገልፀዋል።
በዚህም መሠረት ውይይቱ የሚካሄደው በቡድን ሲሆን፣ እያንዳንዳቸው 50 ሰዎችን የሚይዙ 80 ቡድኖች እንደሚዋቀሩና ከእነዚህ 80 ቡድኖች ውስጥ ድሬዳዋ አነስተኛ የተሳታፊ ቁጥር እንደሚኖራት ጠቅሰዋል፡፡
ኮሚሽኑ ለብሔራዊ ጉባኤው የማይበቁ እና በክልል ደረጃ የሚፈቱ አጀንዳዎችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሉበት ለክልል አመራሮች ለማስረከብ ዝግጅት ማጠናቀቁን ዶ/ር አምባዬ አብራርተዋል፡፡
በሚዋቀሩት ቡድኖች ውስጥ የእያንዳንዱ ማህበረሰብ ተወካዮች እንደሚኖሩና እያንዳንዱ ቡድን መግባባት ላይ እንዲደርስ የሚያግዝ የባለሙያዎች ቡድን እንደሚኖርም ተመልክቷል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ