ሚያዚያ 15 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)ባለፈው የፈረንጆች አመት ቤሊንግካት (Bellingcat) የተባለው የምርመራ ተቋም ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት የአሜሪካ አየር ሃይል አባላት ለፈተና ለመዘጋጀት የተጠቀሙባቸው የዲጂታል ማጥኛ ካርዶች (flashcards) እጅግ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግባቸውን የኑክሌር ሚስጥሮች ለሕዝብ ግልጽ አድርገዋል።
ይህ የደህንነት ጉድለት በአውሮፓ ውስጥ በሚገኙ ስድስት ወታደራዊ ካምፖች ውስጥ ያሉ የኑክሌር ማከማቻዎችን ዝርዝር መረጃ ያካተተ ሲሆን በተለይም በጣሊያን (አቪያኖ እና ጌዲ)፣ በቱርክ (ኢንቺርሊክ)፣ በኔዘርላንድስ (ቮልከል)፣ በቤልጂየም (ክላይን ብሮገን) እና በጀርመን (ቡቸል) የሚገኙ መጋዘኖችን ይነካል።
በእነዚህ ካምፖች ውስጥ በድምሩ 100 የሚሆኑ B61-3 እና B61-4 የተሰኙ ታክቲካዊ የኑክሌር ቦምቦች እንደሚገኙ ይታመናል። ይሁን እንጂ ወታደሮቹ በፈጠሩት ስህተት የትኞቹ መጋዘኖች “ትኩስ” (ቦምብ ያለባቸው) እና የትኞቹ “ቀዝቃዛ” (ባዶ) እንደሆኑ እንዲሁም የደህንነት ካሜራዎች ያሉባቸው ቦታዎች፣ ልዩ የባጅ መታወቂያዎች እና የጭንቀት ጊዜ የይለፍ ቃላት ጭምር በኢንተርኔት ላይ ለሁሉ ተጋልጠዋል።
ቦምቡን በሀይል ማፈንዳት ይቻላል?
ምንም እንኳን መረጃው ቢጋለጥም የB61 ቦምቦችን ያለፈቃድ ማፈንዳት የማይቻል መሆኑ ይነገራል። እነዚህ ቦምቦች “Permissive Action Link (PAL)” የተባለ የ12 አሃዝ ሚስጥራዊ ኮድ የሚጠይቁ ሲሆን የተሳሳተ ኮድ በተደጋጋሚ ከተሞከረ የቦምቡን ኤሌክትሮኒክስ በማቃጠል ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ ያደርገዋል።
ይህ ክስተት በዲጂታል ዘመን ሚስጥራዊ መረጃዎችን የመጠበቅ ተግዳሮት ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ትልቅ ማሳያ ሆኖ አልፏል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ