መጋቢት 30 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በኢራን ከተካሄደው “ውጤታማ የመንግሥት ለውጥ” በኋላ ከአዲሱ የሀገሪቱ አመራር ጋር በቅርበት እንደምትሠራ በይፋ አስታውቀዋል። ፕሬዝዳንቱ በትሩዝ ሶሻል (Truth Social) ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ከኢራን ጋር በሚደረገው አዲስ ስምምነት መሠረት “ከእንግዲህ የዩራኒየም ማበልጸግ ሥራ አይኖርም” ሲሉ በፅኑ ገልጸዋል።
እንደ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ማብራሪያ፣ አሜሪካ ከኢራን ጋር በመተባበር በጥልቀት ተቀብረው የሚገኙ የኒውክሌር ግብዓቶችን (Nuclear Dust) የማውጣትና የማስወገድ ሥራ ትሠራለች። ይህ ሂደትም በጠፈር ኃይል (Space Force) ሳተላይቶች አማካኝነት ጥብቅ ክትትል እየተደረገበት መሆኑን ጠቁመዋል። ፕሬዝዳንቱ አክለውም፣ ጥቃት ከተፈጸመበት ዕለት ጀምሮ እስካሁን ምንም ዓይነት ንብረት እንዳልተነካ እና ሁኔታው በቁጥጥር ስር መሆኑን አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም አሜሪካ ከኢራን ጋር በተጣሉ የታሪፍ እና የኢኮኖሚ ማዕቀቦች ዙሪያ ድርድር እያደረገች መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፣ ካቀረቧቸው 15 ዋና ዋና የድርድር ነጥቦች መካከል በአብዛኛዎቹ ላይ ቀደም ብሎ ስምምነት ላይ መደረሱን ይፋ አድርገዋል። ይህ አዲስ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ በመካከለኛው ምስራቅ ለዓመታት የዘለቀውን የኒውክሌር ስጋት እና ውጥረት ለመቀነስ ትልቅ ተስፋ የጣለ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ