መጋቢት 25 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)ጂያንሉካ ፕሬስቲያኒ በቪኒሲየስ ጁኒየር ላይ የዘረኝነት ስድብ ሰድቧል በሚል የቀረበበትን ክስ በአዲስ ቃለ መጠይቅ ያስተባበለ ሲሆን፤ “ያለ ጥፋቴ ነው የተቀጣሁት” ሲልም ተናግሯል።
በፖርቹጋል ሊዝበን በተደረገው የሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ማጣሪያ ጨዋታ፣ የሪያል ማድሪዱን ኮከብ ቪኒሲየስ ጁኒየርን በዘረኝነት ሰድቧል በሚል በዩኤፋ (UEFA) የታገደው የቤንፊካው አጥቂ ጂያንሉካ ፕሬስቲያኒ ድርጊቱን መፈጸሙን በጽኑ አስተባብሏል። አርጀንቲናዊው ተጫዋች በሰጠው አዲስ ቃለ መጠይቅ፤ ምንም ዓይነት ተጨባጭ ማስረጃ በሌለበት ሁኔታ በአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር (ዩኤፋ) የተጣለበት ጊዜያዊ እግድ፣ እሱንና ቤተሰቡን ለከፍተኛ ሥነ-ልቦናዊ ጫና እንደዳረጋቸው ገልጿል።
ቪኒሲየስ ግብ ካስቆጠረ በኋላ በተፈጠረው ግጭት ወቅት የቀረበበት የዘረኝነት ክስ ተገቢ እንዳልሆነና ዩኤፋ ውሳኔ ለማሳለፍ መቸኮሉን ተችቷል። ፕሬስቲያኒ በዚህ እግድ ምክንያት ቤንፊካ በሪያል ማድሪድ ተሸንፎ ከሻምፒዮንስ ሊግ በወጣበት ወሳኝ የማጣሪያ ጨዋታ ላይ ሳይሰለፍ ቀርቷል።
ጂያንሉካ ፕሬስቲያኒ በዘንድሮው የ2025/26 የውድድር ዘመን በቤንፊካ ቤት በሁሉም ውድድሮች 26 ጨዋታዎችን አድርጎ 9 ግቦችን ሲያስቆጥር፣ 5 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን ደግሞ አመቻችቶ በማቀበል ለክለቡ ውጤታማነት ትልቅ ድርሻ አበርክቷል። በፖርቹጋል ሊጋ ኖስ 85.4 በመቶ የተሳካ ኳስ የማቀበል ስኬት ያለው ሲሆን፤ በአማካይ በአንድ ጨዋታ 2.2 ቁልፍ ኳሶችን እና 3.8 ስኬታማ በሆነ መንገድ ተከላካዮችን የማለፍ (dribbling) አኃዝ አለው። በሻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይም 2 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በተለይም በሜዳው ባደረጋቸው ጨዋታዎች 64 በመቶ የሚሆኑት ሙከራዎቹ ኢላማቸውን የጠበቁ ነበሩ።
ተጫዋቹ በጨዋታው ወቅት ከኪሊያን ምባፔ ጋር የቃላት ልውውጥ ማድረጉን ገልጾ፤ ምባፔ “ዘረኛ” ብሎ እንደሰደበውና ይህም ለአርጀንቲናውያን እንደ ተራ ስድብ እንደሚቆጠር ተናግሯል። ፕሬስቲያኒ ቪኒሲየስን “ዝንጀሮ” በሚል ስድብ አልሰደብኩም ሲል በድጋሚ ያረጋገጠ ሲሆን፤ “እውነትን የሚያውቁ ሰዎች ሁሉ ከጎኔ መሆናቸው ይበቃኛል” ብሏል። የቤንፊካ አመራሮችም ተጫዋቻቸውን ለመከላከል ለዩኤፋ ይግባኝ ለማቅረብ እየተዘጋጁ እንደሆነ ታውቋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ