መጋቢት 25 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በመካከለኛው ምስራቅ ለዓመታት ሲንተከተክ የቆየው ፍጥጫ አሁን ወደማይመለስበት እና እጅግ አደገኛ ወደሆነው ቀጥተኛ ጦርነት ምዕራፍ መሸጋገሩ ተሰምቷል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎች እርስ በእርስ እየተለዋወጡት ያለው ጠንካራ የዛቻ ቃል ዓለምን በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ጥሏታል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ፣ አሜሪካ በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በኢራን ላይ “በጣም ጠንካራ” የተባለ ወታደራዊ ጥቃት ለመሰንዘር ዝግጁ መሆኗን በይፋ ተናግረዋል። ይህ በትራምፕ በኩል የተሰጠው “የሳምንታት ቀጠሮ” አሜሪካ በቀጠናው ያላትን ወታደራዊ አቋም ወደ ከፍተኛ ጥቃት ለመቀየር መወሰኗን የሚያሳይ መሆኑ ተነግሯል። በተለይም በቅርቡ በፔንታጎን ከፍተኛ የጦር መሪዎች ላይ የተወሰደው የጅምላ ስንብት፣ ፕሬዝዳንቱ ለዚህ ወሳኝ ጥቃት ጦሩን እያስተካከሉ መሆኑን እንደሚያሳይ ወታደራዊ ተንታኞች እየገለጹ ይገኛሉ።
በሌላ በኩል፣ ኢራን ለአሜሪካ በሰጠችው እጅግ አስደንጋጭ ምላሽ፣ ማንኛውም የአሜሪካ የምድር ጦር ወደ ግዛቷ የሚገባ ከሆነ “አንድም ሰው በሕይወት አይተርፍም” ስትል በይፋ ዝታለች። የኢራን አብዮታዊ ዘብ (IRGC) ከፍተኛ መኮንኖች እንደገለጹት፣ ኢራን ማንኛውንም ዓይነት ወረራ ለመቀልበስ የሚያስችሉ “ሚስጥራዊ የጦር መሣሪያዎችን” አዘጋጅታለች። “የአሜሪካ ወታደሮች ወደ ኢራን ምድር ከገቡ መቃብራቸውን እዚያው ይቆፍራሉ” የሚለው የኢራን ጠንካራ መልዕክት፣ ቀጠናው ወደ ከፋ ደም መፋሰስ እያመራ መሆኑን ያመላክታል።
በአሁኑ ወቅት በፋርስ ባሕረ ሰላጤ እና በቀይ ባሕር አካባቢ የሚገኙ የአሜሪካ የጦር መርከቦች እንዲሁም የኢራን የሚሳኤል ክፍሎች በከፍተኛ ንቃት ላይ ይገኛሉ። ይህ የሁለቱ ኃያላን አገራት የቃላት ጦርነት ወደ ተግባር ከተቀየረ፣ ለረጅም ጊዜ የሚቆይና መላውን ዓለም ሊያዳርስ የሚችል መጠነ ሰፊ ቀውስ ሊፈጥር እንደሚችል እየተሰጋ ነው።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ