መጋቢት 25 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) ሊቨርፑል በ125 ሚሊዮን ፓውንድ የእንግሊዝ የዝውውር ክብረ ወሰንን በመስበር ያስፈረመው፣ ትውልደ ኤርትራዊው ስዊድናዊ አጥቂ አሌክሳንደር ኢሳክ ከገጠመው ከባድ ጉዳት አገግሞ ዛሬ ከቡድኑ ጋር ልምምድ እንደሚጀምር አሰልጣኝ አርኔ ስሎት አረጋግጠዋል።
ኢሳክ ባለፈው ታህሳስ ወር ከቶተንሃም ጋር በተደረገ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ላይ ግብ እያስቆጠረ በነበረበት ወቅት በደረሰበት የቁርጭምጭሚት አጥንት ስብራት (fibula fracture) ምክንያት ለወራት ከሜዳ ርቆ መቆየቱ ይታወሳል። አሰልጣኙ ተጫዋቹ ላለፉት አራት ወራት ጠንካራ የማገገሚያ ስራዎችን ሲሰራ እንደነበር ገልጸው፣ ወደ ቡድን ልምምድ መመለሱ ለተጫዋቹም ሆነ ለክለቡ ትልቅ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
አሌክሳንደር ኢሳክ በዘንድሮው የ2025/26 የውድድር ዘመን እስከ ጉዳቱ ድረስ በሊቨርፑል ቤት በሁሉም ውድድሮች 16 ጨዋታዎችን አድርጎ 3 ግቦችን ብቻ ነው ማስቆጠር የቻለው። ከነዚህም መካከል ሁለቱ በፕሪሚየር ሊግ ሲሆኑ፣ አንዱ ደግሞ በካራባኦ ካፕ የተቆጠረ ነው። በተጨማሪም በሊቨርፑል ማልያ አንድ ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል። ተጫዋቹ ሊቨርፑልን ከተቀላቀለ በኋላ በቋሚነት መሰለፍ የቻለው በ10 ጨዋታዎች ላይ ብቻ ሲሆን፤ ይህም ለ508 ደቂቃዎች ያህል ብቻ ነው። ባለፈው ታህሳስ ወር ያጋጠመው የቁርጭምጭሚት አጥንት ስብራት ለ4 ወራት ከሜዳ ሲያርቀው፣ በዚህም ምክንያት 21 ያህል ጨዋታዎች አምልጠውታል።
ምንም እንኳን ተጫዋቹ ዛሬ ልምምድ ቢጀምርም፣ አሰልጣኝ አርኔ ስሎት እንደገለጹት ለረጅም ጊዜ ከሜዳ በመራቁ ምክንያት ወዲያውኑ ወደ ጨዋታ ይመለሳል ተብሎ አይጠበቅም። ይሁን እንጂ በሚቀጥለው ሳምንት በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ከፈረንሳዩ ሀያል ክለብ ፓሪስ ሳን ዠርሜን (PSG) ጋር ለሚደረገው ፍልሚያ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ሊሰለፍ እንደሚችል ተገምቷል። የኢሳክ መመለስ ሊቨርፑል በቀሪዎቹ ሁለት ወራት በሻምፒዮንስ ሊግ እና በኤፍኤ ካፕ ለሚያደርጋቸው ወሳኝ ጨዋታዎች ትልቅ አቅም እንደሚሆን ይታመናል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ