መጋቢት 25 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ፤ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲሁም ተጠቃሚነት በተመለከተ ከሚዲያ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
በሀገራችን ብሎም በከተማችን የሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እስካሁን በሚፈለገው ልክ አልተረጋገጠም ያሉት፤ በአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ዘርፍ ተሳትፎ፣ ማብቃትና ተጠቃሚነት ዳይሬክተር ወይዘሮ ስፍራሽ አልማው ናቸው። በተያዘው የበጀት ዓመትም ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው 26 ሴቶች የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተመላክቷል።
ቢሮው፤ የሚዲያ አካላት የሴቶችን ተሳትፎ የተመለከቱ ጉዳዮችን አጀንዳ አድርገው ከመሥራት አኳያ ውስንነቶች እንዳሉባቸው አመላክቷል። በመሆኑም በመገናኛ ብዙኃን አዋጁ ላይ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች ታሳቢ በማድረግ ሊሠሩ እንደሚገባ ተገልጿል።
በተጨማሪም በመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችና ኃላፊዎች በፆታ ላይ የተመሰረተ መድልዎ ያላቸውን የማኅበራዊም ሆነ የብሮድካስት ፕሮግራሞችን ሊሞግቱ እንደሚገባ በውይይቱ ላይ ተነስቷል።
ሴቶችን የዘገባ ምንጭ በማድረግ የእኩልነት መርህን ማረጋገጥ የመንግሥት ተቋማት ብቻ ሳይሆን የሚዲያ ተቋማትም ሥራ መሆን እንዳለበት ተጠቁሟል። ተቋማቱም ሚዲያዎች ለሚሠሯቸው የምርመራና ሌሎች ዘገባዎች አስፈላጊውን ትብብር ሊያደርጉ እንደሚገባ ተመላክቷል።
በውይይቱ ላይ ከተሳተፉ የሚዲያ አካላት በኩል፤ ተቋማት መረጃ በሚፈለግበት ወቅት ፈቃደኛ የመሆንና በሰዓቱ የመስጠት ውስንነት እንዳለባቸው ተነስቷል። ቢሮው በበኩሉ ወደፊት ሴቶችን፣ ሕፃናትንና አረጋውያንን የተመለከቱ መረጃዎችን በቅንነትና በወቅቱ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ