መጋቢት 24 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኤግዚቢሽን አውደ ርዕይ “ቃል በተግባር፤ ከምርጫ እስከ ምርጫ” በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 23 እስከ መጋቢት 25 ቀን 2018 ዓ.ም በኦሮሚያ ባህል ማዕከል እንደሚካሄድ ተገልጿል።
ባለፉት አምስት ዓመታት በመንግሥት የታቀዱና የተከናወኑ መጠነ ሰፊ የልማት ሥራዎችን ለሕዝብ ይፋ የሚያደርግ አውደ ርዕይ መሆኑን የተናገሩት የፌዴራል መንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ደሲሳ ናቸው።
ሚኒስትር ዴኤታው እንዲህ ያሉ መድረኮች መንግሥት ለሕዝብ የገባውን ቃል በተግባር ማከናወኑን በአካል ለማረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ አላቸው ብለዋል።
“ቃል በተግባር፤ ከምርጫ እስከ ምርጫ” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ኤግዚቢሽን፤ የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ተቋማት የመንግሥት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ለሕዝብ ተደራሽ የማድረግ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነም ተናግረዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም አውደ ርዕዩ ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገሪቱ የተመዘገቡ ለውጦችን ሕዝቡ በበቂ መረጃ እንዲገነዘብና በቀጣይ በሚካሄደው ምርጫ ሚዛናዊ ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ያግዛል ብለዋል።
መገናኛ ብዙኃንና የኮሚኒኬሽን ተቋማት የሀገሪቱን የታሪክ ምዕራፍና የኢኮኖሚ ዕድገት ለሕዝብ በማሳየት ረገድ የሚጠበቅባቸውን ሚና አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አስተላልፈዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት ከግብርናው ዘርፍ በተጨማሪ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ በተፈጥሮ ጋዝ ልማት፣ በቱሪዝም መዳረሻዎች ማስፋፋት እንዲሁም በከተሞች ውበትና ልማት ረገድ የተሠሩ ሥራዎች ኢትዮጵያን ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ያሸጋገሩ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው አክለው ገልጸዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ