መጋቢት 18 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር (UEFA) የፖርቹጋሉ ክለብ ቤንፊካ በዘረኝነት ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ቅጣት እንደተላለፈበት አስታውቋል። ማኅበሩ በቅርቡ ቤንፊካ ከሪያል ማድሪድ ጋር ባደረጉት የቻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ወቅት በታየው የዘረኝነት ድርጊት ምክንያት፣ በፖርቹጋሉ ክለብ ላይ የገንዘብ እና የእግድ ቅጣት አስተላልፏል።
በጨዋታው ወቅት የሪያል ማድሪዱ የክንፍ መስመር ተጫዋች ቪኒሲየስ ጁኒየር፣ በቤንፊካው አርጀንቲናዊ ተጫዋች ጂያንሉካ ፕሬስቲያኒ የዘረኝነት ስድብ እንደደረሰበት ለዳኛው ካመለከተ በኋላ ጨዋታው ለተወሰነ ደቂቃ ተቋርጦ ነበር። በጉዳዩ ላይ በርካታ ውዝግቦች የተነሱ ሲሆን፣ ኪሊያን ምባፔም ተጫዋቹ “ጦጣ” እያለ አምስት ጊዜ ሲሳደብ መስማቱን መግለጹን ተከትሎ የአውሮፓ እግር ኳስ አወዳዳሪ አካል ምርመራ ሲያካሄድ ቆይቷል። ተቋሙ ባወጣው መግለጫ መሠረት፣ የቤንፊካ ደጋፊዎች በጨዋታው ባሳዩት ያልተገባ ባህሪ ምክንያት ክለቡ 40,000 ዩሮ እንዲቀጣ ተወስኗል።
ከዚህ በተጨማሪም ክለቡ በቀጣዩ የአውሮፓ ውድድር በሜዳው በሚያደርገው ጨዋታ በስታዲየሙ ውስጥ የሚገኙ 500 መቀመጫዎችን ክፍት እንዲያደርግ የታዘዘ ሲሆን፣ ይህ የስታዲየም እግድ ለአንድ ዓመት የሚቆይ መሆኑ ተገልጿል። ከዘረኝነት ድርጊቱ በተጨማሪ ቤንፊካ ደጋፊዎቹ ወደ ሜዳ ቁሶችን በመወርወራቸው እና ሌዘር በመጠቀማቸው ምክንያት ተጨማሪ 33,000 ዩሮ የገንዘብ ቅጣት ተጥሎበታል። በሌላ በኩል የክለቡ ረዳት አሰልጣኝ ፔድሮ ሉዊስ ፌሬራ ማቻዶ ተገቢ ያልሆነ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በማሳየታቸው ለአንድ ጨዋታ ታግደዋል።
የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ እና የቼልሲ አሰልጣኝ ሆሴ ሞውሪንሆ በወቅቱ በሰጡት አስተያየት፣ በሁለቱ ተጫዋቾች መካከል ስለተፈጠረው ነገር ገለልተኛ መሆን እንደሚፈልጉ መናገራቸው ይታወሳል። ሪያል ማድሪድ በሁለቱ ጨዋታዎች ድምር ውጤት 3 ለ 1 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ የቻምፒዮንስ ሊግ ዙር ያለፈ ሲሆን፣ በደርሶ መልስ መርሃ-ግብሩ የዘረኝነት ጥቃት ሰለባ የነበረው ብራዚላዊው ኮከብ ቪኒሲየስ ጁኒየር ግብ ማስቆጠሩ ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ አፉን ሸፍኖ የዘረኝነት ስድብ ተሳድቧል ተብሎ በብዙዎች የሚታመነው አርጀንቲናዊው ተጫዋች ፕሬስቲያኒ ምንም አይነት ቅጣት ሳይተላለፍበት መቅረቱ መነጋገሪያ ሆኗል። በመፈክር እና በጽሁፍ ብቻ ዘረኝነትን ከእግር ኳስ ማራቅ እንደማይቻል የገለጹ ወገኖች ዩኤፋ ጠንከር ያለ ቅጣት ከመስጠት መቆጠቡ “ጥርስ የሌለው ተቋም” መሆኑን ያሳያል ሲሉ ተችተዋል። በአንጻሩ ደግሞ ፕሬስቲያኒን ለመቅጣት የሚያስችል በቂ ማስረጃ ባለመገኘቱ ሊሆን እንደሚችል አስተያየት የሚሰጡ ቢኖሩም፣ በርካታ የእግር ኳስ ቤተሰቦች ግን ተጫዋቹ ሳይቀጣ ማለፉን እያወገዙት ይገኛሉ።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ