መጋቢት 16 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)ፈረንሳዊው የአማካይ መስመር ተጫዋች ዲሚትሪ ፓዬት ለ21 ዓመታት የዘለቀውን ስኬታማ የእግር ኳስ ዘመን በይፋ ማክተሙን አስታውቋል። ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ህይወቱን በፈረንሳዩ ናንት ክለብ የጀመረው ፓዬት፤ በቆይታውም በሴንት ኤቲየን፣ ሊል፣ ኦሎምፒክ ማርሴ፣ ዌስትሃም እና ቫስኮ ዳ ጋማ ባሉ ታዋቂ ክለቦች ውስጥ የማይረሳ አሻራውን ጥሎ አልፏል።
በተለይም በማርሴይ በነበረው ቆይታ በሁለት የተለያዩ አጋጣሚዎች 326 ጨዋታዎችን በማድረግ 78 ግቦችን አስቆጥሮ 95 ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል። በፈረንሳይ ሊግ 1 ታሪክም ከፍተኛ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ስሙ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ተጫዋች ነው።
ዲሚትሪ ፓዬት በዘንድሮው የ2025/26 የውድድር ዘመን በብራዚሉ ቫስኮ ዳ ጋማ ቤት 18 ጨዋታዎችን አድርጎ 3 ግቦችን ሲያስቆጥር 4 ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል ከእግር ኳስ ተጫዋችነቱ ተሰናብቷል። ተጫዋቹ ለፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን 38 ጨዋታዎችን አድርጎ 8 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በተለይም በ2016ቱ የአውሮፓ ዋንጫ ላይ ያሳየው አስደናቂ ብቃትና ያስቆጠራቸው ግቦች ምንጊዜም ይታወሳሉ።
በ2016 የባሎን ዶር ደረጃ 17ኛ ሆኖ ማጠናቀቁም በወቅቱ የነበረውን ከፍተኛ ብቃት ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል። ፓዬት በፈጠራ ብቃቱ እና በቅጣት ምት ክህሎቱ በብዙ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ዘንድ ትልቅ አድናቆት የሚሰጠው ተጫዋች ሲሆን፤ ወደፊትም ከሜዳ ውጭ በሌላ ዘርፍ እግር ኳስን ለማገልገል እንደሚዘጋጅ ይጠበቃል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ