መጋቢት 12 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማምረት የሚታወቀው ኦሞዌይ (OMOWAY) ኩባንያ ኦሞ ኤክስ (OMO X) የተሰኘውንና ሚዛኑን በራሱ መጠበቅ የሚችለውን ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክል በብዛት ማምረት መጀመሩን በይፋ አስታውቋል።
ይህም በአለም አቀፍ ደረጃ መሰል ቴክኖሎጂ የታጠቀ የሁለት እግር ተሽከርካሪ ከሙከራ ደረጃ አልፎ ለገበያ እንዲቀርብ በብዛት ሲመረት የመጀመሪያው ያደርገዋል።
ተሽከርካሪው ኦሞ-ሮቦት (OMO-Robot) የተሰኘ የተቀናጀ የቴክኖሎጂ ስርዓት የሚጠቀም ሲሆን ይህም በጠፈር ምርምር ስራዎች ላይ የሚውለውን የጋይሮስኮፕ (Gyroscope) ቴክኖሎጂን የተጠቀመ ነው። ሞተር ሳይክሉ በቆመበትም ሆነ በጣም በዝግታ በሚጓዝበት ወቅት ሳይወድቅ ቀጥ ብሎ እንዲቆም የሚያስችለው ይህ ቴክኖሎጂ በተለይ ለጀማሪ አሽከርካሪዎች እና በትራፊክ መጨናነቅ ውስጥ ለሚጓዙ ምቹ እንደሆነ ተገልጿል።
ሞተር ሳይክሉ የመውደቅ አዝማሚያ ሲያሳይ በሰከንድ ውስጥ በራሱ ጊዜ የሰውነት ክፍሉን በማመጣጠን ሚዛኑን ይጠብቃል።
እንደ ኩባንያው መግለጫ ከሆነ የኦሞ ኤክስ ቅድመ ትዕዛዝ በፈረንጆቹ ሚያዝያ ወር መጨረሻ ላይ የሚጀመር ሲሆን የመጀመሪያዎቹ ምርቶች ደግሞ በግንቦት ወር መጨረሻ በኢንዶኔዢያ ጃካርታ ለደንበኞች መሰራጨት ይጀምራሉ። ይህ አዲስ የፈጠራ ውጤት የትራንስፖርት ዘርፉን ወደ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) የታገዘ የሮቦቲክስ ዘመን የሚያሸጋግርና የአሽከርካሪዎችን ደህንነት በከፍተኛ ደረጃ የሚያረጋግጥ እንደሆነ ተነግሮለታል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ