መጋቢት 09 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ታዳጊ ልጃቸውን ኪም ጁ ኤን በማስከተል በሀገሪቱ ስልታዊ የክሩዝ ሚሳኤል ሙከራ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ መገኘታቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ይህኛው ሙከራ ካለፈው የሚለየው ሚሳኤሎቹ ‘ቾይ ህዮን’ ከተሰኘችው የባህር ኃይል አውዳሚ መርከብ ላይ የተተኮሱ መሆናቸው ሲሆን ይህም ሀገሪቱ ከመሬት በተጨማሪ ከባህር ላይ ጥቃት የመሰንዘር አቅሟን ማሳደጓን ያረጋገጠ ክንውን ሆኗል።
ሚሳኤሎቹ በሰሜን ኮሪያ ምዕራባዊ የባህር ጠረፍ ላይ የተቀመጡ ኢላማዎችን በትክክል መምታታቸው የተገለጸ ሲሆን መሪው ኪም ጆንግ ኡንም የዚህ ጥቃት ዓላማ የባህር ኃይሉን የማጥቃት አቅም በተግባር ለማሳየትና አስተማማኝ የሆነ የኒውክሌር ጦርነት መከላከያ አቅምን ይበልጥ ለማጠናከር መሆኑን ተናግረዋል።
በወታደራዊ መድረኮች ላይ በተደጋጋሚ እየታየች ያለችው የ13 ዓመቷ የመሪው ልጅ መገኘትም የሀገሪቱን ቀጣይ መሪነት ትረከባለች የሚል ግምትን በዓለም አቀፍ ተንታኞች ዘንድ በሰፊው እያሳደረ ይገኛል።
ይህ የሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራ የተከናወነው አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ የሚያካሂዱትን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ተከትሎ ሲሆን ሰሜን ኮሪያ ይህንን ልምምድ ሀገሪቱን ለመውረር የሚደረግ ዝግጅት ስትል በድጋሚ ኮንነዋለች።
ካለፈው ሙከራ በተለየ መልኩ በዚህኛው ሒደት ላይ የባህር ኃይሉን ስልታዊ የበላይነት ለማሳየት ትኩረት የተሰጠው ሲሆን የታዳጊዋ ኪም ጁ ኤ በወታደራዊው መስክ ያላት ተሳትፎም ከመቼውም ጊዜ በላይ ጎልቶ ታይቷል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ