መጋቢት 08 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በስምንት ዓመቷ ሕይወቷን አደጋ ላይ የሚጥልና በቀን እስከ 150 ጊዜ የሚደርስ የሚጥል በሽታ (seizure) ያጋጥማት የነበረችው ክሪስቲና ሳንታውስ፣ በአሁኑ ወቅት ለብዙዎች ተምሳሌት የሆነ የሕይወት ታሪክ ባለቤት ለመሆን በቅታለች።
በወቅቱ የነበረው ብቸኛ አማራጭ ግማሽ የአንጎል ክፍሏን በቀዶ ጥገና ማስወገድ የነበረ ቢሆንም፣ ውጤቱ ግን ከታሰበው በላይ ስኬታማ ሆኗል።
ክሪስቲና “ራስሙሰን ኤንሴፋላይተስ” (Rasmussen’s Encephalitis) በሚባል የአንጎል በሽታ ትሰቃይ በነበረበት ወቅት፣ መድኃኒቶች ሊፈውሷት ባለመቻላቸው ሐኪሞች ለ14 ሰዓታት የፈጀ አደገኛ ቀዶ ጥገና ለማድረግ ተገደዋል።
ይህ ቀዶ ጥገና ግማሽ የአንጎል ክፍሏን ማስወገድን የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ብዙዎች ወደፊት መደበኛ ሕይወት መምራት እንደማትችል ገምተው ነበር።
ይሁን እንጂ የቀረው የአንጎሏ ክፍል ራሱን በራሱ በማደራጀት (neuroplasticity) የተወገደው የአንጎል ክፍል ይሠራቸው የነበሩ ተግባራትን ጭምር ማከናወን ጀምሯል።
ምንም እንኳን በአንድ በኩል የሰውነት እንቅስቃሴ ውስንነት ቢገጥማትም፣ የማስታወስ ችሎታዋ፣ ስብዕናዋና የማሰብ ብቃቷ ግን ሳይጎዳ መቆየት ችሏል።
ክሪስቲና በሕይወት ለመቆየት ካደረገችው ተጋድሎ ባሻገር፣ በትምህርቷም ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የማስተርስ ዲግሪዋን ማግኘት ችላለች።
በአሁኑ ወቅት የንግግርና ቋንቋ ስፔሻሊስት (Speech-language pathologist) በመሆን መሰል ችግር ያለባቸውን ሰዎች በሙያዋ እያገለገለች ትገኛለች።
ይህ የክሪስቲና የጥንካሬ ታሪክ፣ የሰው ልጅ አእምሮ ያለውን አስገራሚ የመታደስ ብቃትና ተስፋ አለመቁረጥ የሚያስገኘውን ውጤት ለዓለም የሚያሳይ ሆኖ ተመዝግቧል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ