መጋቢት 08 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በፍሎሪዳ ግዛት ማርቲን ካውንቲ በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ የሚገኝ አንድ ታራሚ፣ ለአንድ ሰው የማይታመን በሚባል ጉልበት የብረት ካቴናን በባዶ እጁ በመጠምዘዝ እና በመስበር ማምለጥ መሞከሩ ተሰማ።
የማርቲን ካውንቲ ሸሪፍ ጽህፈት ቤት ይፋ ባደረገው መረጃ እና ምስል መሰረት፣ ግለሰቡ ካቴናውን የሰባበረው ልክ ከፕላስቲክ እንደተሰራ ቁስ በቀላሉ በመጠምዘዝ ነው። የታራሚው ማንነት ባይገለጽም፣ ድርጊቱን የፈጸመው በከፍተኛ የአእምሮ ውጥረት እና መረበሽ ውስጥ በነበረበት ወቅት እንደሆነ ታውቋል።
ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት፣ ሰዎች በከፍተኛ የፍርሃት ወይም የጭንቀት ስሜት ውስጥ ሲሆኑ ሰውነታቸው ከመደበኛው አቅም በላይ የሆነ “ድንገተኛ ጉልበት” ሊያመነጭ ይችላል። ይህ ታራሚም በወቅቱ የነበረበት የውስጥ መረበሽ ለብረት ካቴናው መበጠስ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ተገምቷል።
በወቅቱ በእስር ቤቱ የነበሩ የጸጥታ አባላት ግለሰቡን በፍጥነት በቁጥጥር ስር ያዋሉት ሲሆን፣ በዚህ አጋጣሚ በታራሚውም ሆነ በጸጥታ አካላቱ ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ተብሏል። ጉዳዩ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
ምላሽ ይስጡ