ጥር 05 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)በኢራን ለሁለት ሳምንታት የቀጠለውን መጠነ ሰፊ ተቃውሞ ተከትሎ መንግስት ጥሎት የነበረውን የኮሙኒኬሽን እገዳ በከፊል ማንሳቱ ተገለጸ። ዛሬ ማክሰኞ ጥር 5 ቀን 2018 ዓ.ም በወጡ መረጃዎች መሠረት፣ በዋና ከተማዋ ቴህራን የሚገኙ ዜጎች ለተወሰኑ ደቂቃዎች ወደ ውጭ አገራት የስልክ ጥሪዎችን ማድረግ ችለዋል። ይህ እርምጃ የተወሰደው ባለስልጣናቱ ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ ስልክን ጨምሮ ሁሉንም የኮሙኒኬሽን መስመሮች ዘግተው ከቆዩ በኋላ ነው።
የስልክ አገልግሎቱ በከፊል ቢጀመርም፣ የኢንተርኔት አገልግሎት እና የጽሁፍ መልዕክት አሁንም እንደተቋረጡ ይገኛሉ። የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና የኔትብሎክስ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ የኢራን መንግስት ኢንተርኔቱን ዘግቶ የቆየው የጸጥታ ኃይሎች በተቃዋሚዎች ላይ የሚወስዱትን የኃይል እርምጃ ዓለም እንዳያየው ለመሸፈን ነው። በነዚህ ቀናት ውስጥ በተካሄደው ግጭት የሟቾች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን እና ከ600 በላይ ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።
በአሁኑ ወቅት በቴህራን የሚገኙ ነዋሪዎች ወደ ውጭ መደወል ቢችሉም፣ ከውጭ ወደ ኢራን የሚደረጉ ጥሪዎች ግን አሁንም አይሰሩም። ይህም አገልግሎቱ ገና ሙሉ በሙሉ አለመመለሱን እና የቁጥጥር ስራው መቀጠሉን ያሳያል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢራን መንግስት የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብት እንዲያከብር እና ኢንተርኔቱን በአስቸኳይ እንዲከፍት ጥሪያቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ ኢንተርኔቱ በቅርቡ ሊመለስ እንደሚችል ፍንጭ ቢሰጡም፣ ትክክለኛው ጊዜ ግን እስካሁን አልታወቀም። ተቃውሞው በኢራን የገንዘብ ምንዛሬ መውደቅ እና በኑሮ ውድነት ሰበብ ቢጀመርም፣ አሁን ግን የመንግስት ለውጥ ወደ መጠየቅ ተሸጋግሮ በአገሪቱ 46 ከተሞች ውስጥ ተስፋፍቶ ይገኛል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63 (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ