ጥር 05 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የቻይና ሳይንቲስቶች በዓለም የመጀመሪያ የሆነውንና ፅንስን በሰው ሰራሽ ማህፀን ውስጥ ተሸክሞ በሰላም መገላገል የሚችል የእርግዝና ሮቦት እያበለጸጉ መሆኑ ተዘግቧል፡፡ በጓንግዙ በሚገኘው የካይዋ ቴክኖሎጂ ኩባንያ አማካኝነት በዶክተር ዣንግ ኪፌንግ የሚመራው ይህ ፕሮጀክት፣ የመጀመሪያውን የሙከራ ሮቦት በያዝነው የ2026 የፈረንጆቹ ዓመት ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ አዲስ ቴክኖሎጂ ፅንሱ በሰው ሰራሽ ማህፀን ውስጥ እንዲያድግ የሚያደርግ ሲሆን፣ ለፅንሱ አስፈላጊ የሆኑ አልሚ ምግቦችም በልዩ ቱቦ አማካኝነት እንዲደርሱት ይደረጋል። ምንም እንኳን የፅንስ መፈጠር ሂደት እንዴት እንደሚከናወን ዝርዝር መረጃዎች ባይገለጹም፣ የሮቦቱ ዋጋ በግምት 100 ሺህ ዩዋን (ወደ 14 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ገደማ) እንደሚሆን ተገምቷል።
ይህ ቴክኖሎጂ በተፈጥሮ ልጆችን መውለድ ለማይችሉ ጥንዶች እንደ ትልቅ ተስፋ ቢታይም፣ በሌላ በኩል ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሥነ-ምግባር ክርክሮችን ቀስቅሷል። በተለይም በልጁ እና በወላጆቹ መካከል የሚኖረው ስሜታዊ ትስስር፣ የህጻኑ ስነ-ልቦናዊ ሁኔታ እና የወላጆች ፈቃድ ዙሪያ ያሉ ጉዳዮች በሳይንቲስቶች እና በሃይማኖት መሪዎች ዘንድ ጥያቄዎችን እያስነሱ ይገኛሉ።
ምንም እንኳን ፕሮጀክቱ በቴክኖሎጂው ዓለም ትልቅ ስኬት ተደርጎ ቢወሰድም፣ በሰው ልጅ የተፈጥሮ የመውለድ ሂደት ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ እና ወደፊት ሊከተሉ የሚችሉ ማህበራዊ ቀውሶች አሁንም አነጋጋሪነታቸው እንደቀጠለ ነው።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63 (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ