ሙሉ ፕሮግራሙን ለማዳመጥ ቀጣዩን ሊንክ ይጫኑ
ጉዳያችሁን ጉዳያችን አድርገን፣ እልባት ያገኝ ዘንድ መፍትሔ በምናፋልግበት የ”ሞግዚት” ጥንቅራችን ዛሬ አንድ ወቅታዊ ጉዳይን ልንመለከት ወደናል።
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04፣ የቤት ቁጥር 18/22 የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪ የነበሩት መቶ አለቃ ካሳኤ እንዳለ፤ ከስምንት ወራት በፊት ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ሕይወታቸው ያልፋል። መቶ አለቃ ካሳኤ በሕይወት በነበሩበት ወቅት የሚኖሩት ብቻቸውን እንደነበርና የሚጠይቃቸው የቅርብም ሆነ የሩቅ ዘመድ እንዳልነበራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
ሟቹ ይኖሩበት የነበረው ቤት፣ መንግሥት በውትድርና ዘመናቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና በመስጠት በልዩ ሁኔታ የሰጣቸው ባለ አንድ መኝታ (ስቱዲዮ) የጋራ መኖሪያ ቤት ነበር። መቶ አለቃ ካሳኤ በድንገተኛ ሕመም ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ተባብረው ሥርዓተ ቀብራቸው እንዲፈጸም አድርገዋል። ሟች ልጅ፣ ሚስትም ሆነ የቅርብ ዘመድ ስለሌላቸው፣ በወቅቱ ይኖሩበት የነበረው ቤት በፖሊስ እንዲታሸግ መደረጉን ነዋሪዎች ያስታውሳሉ።
ይሁን እንጂ ከስድስት ወራት በኋላ፣ ቀደም ሲል ጎረቤታቸው የነበረች አንዲት ግለሰብ “ባለቤታቸው ነበርኩ” በማለት የ”ነፍስ ይማር” ቅመሱ ጥሪ ለጎረቤቶቿ ታቀርባለች። ጥሪው የቀረበላቸው ጎረቤቶች ጉዳዩ ግራ እንደተጋባቸውና ድንጋጤ እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ። መቶ አለቃ ካሳኤ በሕይወት እያሉ አብራቸው የምትኖር ሚስትም ሆነ ዘመድ እንዳልነበራቸው የሚገልጹት ነዋሪዎች፤ ይልቁንም ሟች “ቤቱ ከእኔ በኋላ ለመንግሥት ወይም ለመቄዶንያ ይሁንልኝ” ይሉ እንደነበር ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።
የአደይ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የጊቢ ኮሚቴ አባል፣ ግለሰቧ ቤቱን በሕገ-ወጥ መንገድ የግሏ ለማድረግ እየሞከረች በመሆኑ የሚመለከተው አካል ሊያስቆማት ይገባል ሲሉ ለጣቢያችን ቅሬታ አቅርበዋል። ኮሚቴው አክሎም፣ መቶ አለቃ ካሳኤ በጋራ መኖሪያ ግቢው ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ሲያገለግሉ የነበሩና መልካም ስም ያተረፉ ግለሰብ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት “ባለቤታቸው ነኝ” በማለት ቤቱን ለመውረስ እየተንቀሳቀሰች ያለችው ግለሰብ፤ እንዴት እንደተገኘ ባልታወቀ ሁኔታ የጋብቻ ምስክር ወረቀት ሳይቀር ማውጣቷን ቅሬታ አቅራቢዎች በስጋት ይናገራሉ።
የኮሚቴ አባሏ እንደገለጹት፤ መቶ አለቃ ካሳኤ ሲታመሙ ዘመድ ስለሌላቸው ነዋሪዎች ተባብረው ሕክምና እንዲያገኙ አድርገዋል። ሕይወታቸው ካለፈ በኋላም ምናልባት ዘመድ ቢመጣ በሚል ቤቱ ለስምንት ወራት በፖሊስ ታሽጎ ቢቆይም፣ ድንገት ግለሰቧ የታሸገውን ቤት ከፍታ መግባቷ እንዳስገረማቸው ገልጸዋል። ጉዳዩንም ለወረዳው አስተዳደርና ለፖሊስ ማሳወቃቸውን ተናግረዋል።
መናኸሪያ ሬዲዮም የቀረበውን ቅሬታ መነሻ በማድረግ፣ ግለሰቧን በስልክ ለማነጋገር ሞክሯል። ግለሰቧም የመቶ አለቃ ካሳኤ ባለቤት መሆናቸውን በመግለጽ፣ የቀረበባቸው ቅሬታ መሠረተ ቢስ ነው ሲሉ አጣጥለውታል። ይሁን እንጂ “በትዳር ለስንት ጊዜ ቆያችሁ?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሲሆን፣ በድጋሚ ብንደውልም ስልካቸውን አያነሱም ተብሏል።
የወረዳው የጋራ መኖሪያ ቤት አስተባባሪና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አየለ፣ በቦታው ተገኝተው ሁኔታውን መመልከታቸውን ገልጸዋል። ግለሰቧ ባለቤትነታቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ እንዲያቀርቡ መጠየቃቸውንና በቀጣይም የወረዳው አስተዳደር ጉዳዩን አይቶ እልባት እንደሚሰጠው ተናግረዋል።
የሕግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ በበኩላቸው፣ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 842 መሠረት አንድ ሰው የወራሽነት መብቱን እንዴት ማረጋገጥ እንደሚችል በግልጽ መደንገጉን ያስረዳሉ። ወራሽ ከሌለ ደግሞ በሕግ ቁጥር 846 መሠረት 50 በመቶውን መንግሥት እንደሚወርስ ይገልጻሉ። ኑዛዜን በተመለከተም፣ ሟች በሕይወት እያሉ በውልና ማስረጃ የተረጋገጠ ሰነድ ካላቸው ብቻ ተግባራዊ እንደሚሆን ጠቁመዋል። ግለሰቧ ሚስት መሆኗን ለማረጋገጥ ቢያንስ ለሦስት ዓመታት አብሮ መኖር፣ በሃይማኖት ወይም በባህል ሥነ-ሥርዓት መጋባትና በአካባቢው ነዋሪ ዘንድ እንደ ባልና ሚስት መታወቅ እንዳለባቸው ሕጉ እንደሚያስገድድም አብራርተዋል።
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የወረዳ 4 ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርታ ተፈራ፣ ሟቹን በሚገባ እንደሚያውቋቸው ገልጸው፤ ቀደም ሲል ዘመድም ሆነ ሚስትና ልጅ እንዳልነበራቸው፣ በወረዳው የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብሮች ላይም እንደ ብቸኛ ሰው ይሳተፉ እንደነበር አረጋግጠዋል። ግለሰቧ ቤቱን ሰብረው በመግባታቸው በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑና መንግሥት ጉዳዩን ተከታትሎ እልባት እንደሚሰጥ ቃል ገብተዋል።
ጉዳዩን በቅርበት ተከታትለን የምናቀርብ መሆኑን እየገለጽን፣ ለመረጃው መገኘት የተባበራችሁ አካላትን ሁሉ መናኸሪያ ሬዲዮ ያመሰግናል።
ምላሽ ይስጡ