ሙሉ ፕሮግራሙን ለመስማት ከታች የተያያዘውን ሊንክ ይጫኑ
የአካባቢ ፅዳትና ውበት መጠበቅ ከአይን ማረፊያነት ባለፈ ለሰው ልጅ ጤና፣ ደህንነት እና አጠቃላይ የኑሮ ጥራት መሰረት ነው። ንጹህ አካባቢ ለጤናማ ማህበረሰብ ግንባታ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ፣ በሚመለከተው መስሪያ ቤት በኩል የአካባቢን ደህንነት በማስጠበቅ የተለያዩ ምቹ ሁኔታዎች እንዲዘጋጁ ይደረጋል። ከእነዚህም ተግባራት መካከል በሰው ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮ ምክንያት አካባቢን የሚበክሉ ነገሮችን ማስወገድ አንዱ ነው።
ከዚህ ባሻገር፣ የአካባቢ ፅዳትና ውበት ለዜጎች ጤና አስተማማኝ መሰረት ሲሆን፤ ብክለትን በመከላከል፣ በሽታዎችን በመቀነስ እና ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢ በመፍጠር ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ፈሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎችን በአግባቡ ማስተዳደር፣ የፕላስቲክ ብክለትን መከላከል እንዲሁም ከእንስሳትና ከሰው ልጆች የሚወጡ ተረፈ ምርቶችን በተገቢው መልኩ ማስተዳደር የአካባቢንና የሰውን ጤና ለመጠበቅ እንደሚረዳ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ባህላዊ ወይም ሰው ሰራሽ የሆነ የሰብል እና የእጽዋት ማዳበሪያ (ኮምፖስት) በኢትዮጵያ በከተማም ሆነ በገጠር ለእርሻ ስራ የተለመደ ነው። በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ስራ የአፈርን ጤና ለመጠበቅና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ያለው ፋይዳም ከፍተኛ ነው።
በሌላ በኩል በመዲናዋ ለተተከሉ ዕፅዋትና ለሳር ተብሎ የተዘጋጀው ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ያስከተለው መጥፎ ሽታ፣ ከአካባቢ ብክለት ባለፈ በጤና ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የሚመለከተው አካል እልባት እንዲሰጠው ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ለጣቢያችን አሰምተዋል።
ነዋሪዎቹ አክለውም፣ በከተማዋ ያለውን አረንጓዴ ልማት ለማሳመር ሲባል በመንገድ ዳርና በትራንስፖርት መጠበቂያ አካባቢዎች የተጨመረው ኮምፖስት ከፍተኛ ሽታ እንዳለው ገልጸዋል። ይህ ተግባር ሲከናወንም የሽታው ሁኔታና ለማህበረሰቡ ጤና ያለው ተጽዕኖ ታሳቢ መደረግ እንደነበረበት ይገልፃሉ።
ሽታው በመንገድ ዳር በመሆኑ በተለይም ለህፃናት ተማሪዎችና ጠዋትና ማታ ከስራ ወደ ቤት በሚመለሱ መንገደኞች ላይ፣ በተለይም እንደ አስም ያሉ የመተንፈሻ አካላት ችግር ያለባቸው ሰዎች ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል። በመንግስት በኩል ምንም እንኳን ለልማት ተብሎ የተሰራ ስራ ቢሆንም፣ የዜጎችን ጤና በማይነካ መልኩ መሆን ነበረበት ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
በከተማዋ ውስጥ ባሉ አረንጓዴ ቦታዎች ላይ የሚደፋው ኮምፖስት በመጀመሪያ በማህበረሰቡ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት መኖርና አለመኖሩ መጣራት ነበረበት ያሉት የህግ አማካሪና የአካባቢያዊ መብቶች ተሟጋች አቶ መልካሙ ኡጎ፣ በመተንፈሻ አካላት ላይ ስለሚያደርሰው ጉዳት ህብረተሰቡ ምንም አይነት መረጃ እንደሌለው ገልጸዋል። ሁሉም ሰው ንፁህና ደህንነቱ በተጠበቀ አካባቢ የመኖር መብት እንዳለው ያመላከቱት ተሟጋቹ፤ የተጨመረው ግብዓት ኬሚካል ይሁን ሌላ ነገር የሚታወቅ ነገር ስለሌለ፣ የሚመለከተው አካል የሽታ ልኬት ሰርቶ መጠቀም እንደነበረበትና አሁንም ያለውን የመረጃ ክፍተት ማስተካከል እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ጣቢያችን ስለ ኮምፖስት አዘገጃጀትና ስለ ሽታው ሁኔታ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ከተማ የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን የግብዓትና ቴክኖሎጂ አቅርቦት ቡድን መሪ አቶ ዮሴፍ ደግፈኝ፤ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ሲዘጋጅ ራሱን የቻለ የሚበላሽበት (የሚብላላበት) ጊዜ እንዳለውና ያ ሳይጠበቅ ሲቀር ሽታ ሊያመጣ እንደሚችል ገልጸዋል። አቶ ዮሴፍ አክለውም፣ በተቋማቸው በኩል ለባለሙያዎች አስፈላጊውን ትምህርት እንደሚሰጡ ገልፀው፤ የሽታው ምንጭ ማዳበሪያው ከሰውና ከእንስሳት ተረፈ ምርት ስለሚዘጋጅ ሊሆን እንደሚችልና እሳቸውም ጉዳዩን እንደታዘቡት ገልጸው፣ ከከተማ ጽዳት አስተዳደር ጋር በመሆን የጋራ ክትትል እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
በከተማ ደረጃ 55 ማህበራትን አደራጅተው የከተማ ኮምፖስት እንዲያመርቱ እያደረጉ መሆኑን የገለፁት የአዲስ አበባ ከተማ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙላት ተገኝ፤ ተቋማቸው ለኮምፖስት የሚሆኑ ግብዓቶችን ተጠቅሞ በማምረት ለአረንጓዴ ልማት ቢሮ እንደሚያስረክቡ ገልፀዋል። ሆኖም በተለያዩ አካባቢዎች ስላለው ሽታ ግን መረጃው ከእነሱ ተቋም ውጭ እንደሆነ ገልጸዋል።
መናኸሪያ ሬዲዮ ሽታው በስፋት የሚታይባቸውን አካባቢዎች ጠቅሶ “ከእናንተ እውቅና ውጭ ማን አምጥቶ ጨመረው?” በማለት ላቀረበላቸው ጥያቄ ዳይሬክተሩ ሲመልሱ፤ ተቋማቸው እስካሁን ባደረገው ክትትልና ግምገማ ላይ እንዲህ ያለ ችግር ቀርቦ እንደማያውቅ ገልጸዋል። መናኸሪያ ሬድዮ ከከተማው ነዋሪዎች እንዲሁም ባደረገው ማጣራት በከተማዋ በርካታ ቦታዎች በኮምፖስት ምክንያት የሚመነጭ መጥፎ ሽታ መኖሩን ቢያረጋግጥም፣ የከተማ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲው ግን በግምገማው ወቅት የሚሸት አካባቢ አለመኖሩን ገልጿል። አቶ ሙላት አክለውም በቀጣይ በባለሙያ አሰሳ እንደሚደረግና ከአረንጓዴ ልማት ቢሮ ጋር በመሆን ግብዓቱ ከሌላ ቦታ መጥቶ የተደፋ መሆንና አለመሆኑን እንደሚጣራ ገልፀዋል።
መናኸሪያ ሬዲዮ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጠን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮን በስልክ ለማግኘት ሙከራ ቢያደርግም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ጣቢያችን መረጃ በመስጠት የተባበሩንን እያመሰገነ፣ በቀጣይ የከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮን ሃሳብ አካተን የምንመለስበት ይሆናል።
ምላሽ ይስጡ