ታህሳስ 16 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ) ላንድ ፎር ላይፍ ኢትዮጵያ (Land for Life Ethiopia) “የመሬት አስተዳደርን ማጠናከር እና የመሬት መብቶችን ማረጋገጥ” በሚል መሪ ቃል 3ኛውን የኢትዮጵያ የመሬት ቀን ዛሬ በአዲስ አበባ ኤሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል አክብሯል። በመድረኩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ምሁራን እና የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች ተገኝተው በዘላቂ የመሬት አስተዳደር ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
የላንድ ፎር ላይፍ ኢትዮጵያ የጠቅላላ ጉባኤ ሊቀመንበር ዶ/ር መለሰ ዳምጤ እንደገለጹት፣ ድርጅቱ ሁሉን አቀፍ የመሬት አስተዳደር እንዲሰፍን ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸው፤ ፍትሃዊ ስርዓቶችን መዘርጋት ለማህበረሰቡ ኑሮ መሻሻል ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አስተዳደር እና የጂኦስፓሻል ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ ያላምዘዊድ ደምሴ በበኩላቸው፣ አስተማማኝ የመሬት ይዞታ ለግብርና ለውጥና ለማህበራዊ መረጋጋት ያለውን ፋይዳ በመጠቆም በመንግስትና በሲቪክ ማህበራት መካከል የተቀናጀ ጥረት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
በዕለቱ በዶ/ር ባጫ ከበደ፣ በአቶ ብዙአለም አድማሴ፣ በዶ/ር ዋቅቶሌ ኡማ እና በአቶ ብዙአለም በቀለ አማካኝነት የመሬት አስተዳደር ህጋዊ ማዕቀፎችን፣ የከተማ መሬት ስልቶችን እና የጋራ መሬት ይዞታ ተግዳሮቶችን የሚዳስሱ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የዝግጅቱ ልዩ ትኩረት የነበረው ደግሞ ከቦረና፣ ከረዩ፣ ከሚሴ፣ ባቱ እና ሞጆ የመጡ ገበሬዎችና አርብቶ አደሮች የሰጡት የቀጥታ ምስክርነት ሲሆን፣ ይህም የመሬት ፖሊሲዎች በታችኛው ማህበረሰብ ህይወት ላይ ያለውን ተፅዕኖ አመላክቷል። በመጨረሻም ፍትሃዊ የመሬት አስተዳደርን ለማሳደግ የጋራ እርምጃ አስፈላጊ መሆኑ ላይ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ላንድ ፎር ላይፍ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ2013 ጀምሮ ህዝብን ያማከለ የመሬት አስተዳደር እንዲሰፍንና የማህበረሰብ ተወካዮች በፖሊሲ ቀረጻ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ ላይ የሚገኝ ድርጅት ነው።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63 (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ