ታህሳስ 14 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በሕፃፅና አካባቢው በመጠለያ የሚገኙ ማህበረሰቦች በከፍተኛ የረሃብና የችግር አዙሪት ውስጥ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ላለፉት አራት ወራት ለተጎጂዎች ተብሎ የተላከው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብና በሺዎች የሚቆጠር ኩንታል እህል በትህነግ (TPLF) መዘረፉ ተጋለጠ።
የመናኸሪያ ሬዲዮ 99.1 የውስጥ ምንጮች እንዳረጋገጡት፣ ከጥቅምት ወር ጀምሮ ላለፉት አራት ተከታታይ ወራት ለሕፃፅና አካባቢው ሕዝብ የሚውል ከፍተኛ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ሲላክ ቆይቷል። እንደ ምንጮቹ ገለጻ፣ ላለፉት አራት ወራት የተላከው ድጋፍ ዝርዝር እንደሚከተለው ቀርቧል፦
በመስከረም ወር 2.8 ሚሊዮን ኪሎ ግራም እህል እና 12 ሚሊዮን ብር የተላከ ሲሆን፣ በጥቅምት ወር ደግሞ መጠኑ ጨምሮ 3.1 ሚሊዮን ኪሎ ግራም እህል እና 14.5 ሚሊዮን ብር ደርሷል።
በተመሳሳይ በኅዳር ወር 2.95 ሚሊዮን ኪሎ ግራም እህል እና 13.2 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም አሁን ባለንበት የታኅሣሥ ወር 3.25 ሚሊዮን ኪሎ ግራም እህል እና 15.8 ሚሊዮን ብር ተልኳል።
በአጠቃላይ በአራቱ ወራት ውስጥ 121,000 ኩንታል (12.1 ሚሊዮን ኪሎ ግራም) እህል እና 55.5 ሚሊዮን ብር ለሕፃፅና አካባቢው ሕዝብ ደርሷል።
ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው ድጋፍ በትክክል ለተራበውና ለተቸገረው ሕዝብ ደርሶ ቢሆን ኖሮ፣ በአካባቢው አሁን የሚታየው አስከፊ ረሃብና የዜጎች ስቃይ ሊከሰት አይችልም ነበር ተብሏል።
ይህ መረጃ ይፋ መውጣቱን ተከትሎ፣ የትህነግ አመራሮች የሕዝቡን የዕለት ጉርስ በመንጠቅና ለራሳቸው የፖለቲካና የወታደራዊ ፍጆታ በማዋል ላይ መሆናቸውን ያሳያል ተብሏል።
“ለሕዝብ የተላከው ድጋፍ የት ደረሰ?” የሚለው ጥያቄ በአካባቢው ነዋሪዎችና ጉዳዩን በሚከታተሉ አካላት ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።
መናኸሪያ ሬዲዮ 99.1 የጉዳዩን ሂደት እየተከታተለ ተጨማሪ መረጃዎችን ለተከታታዮቹ የሚያደርስ ይሆናል።
ምላሽ ይስጡ