ታህሳስ 15 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)አሜሪካ እና ኢራን በኒውክሌር ድርድር ዙሪያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ እርስ በርስ ክስ ሲለዋወጡ ዋሉ:: ሁለቱ ሀገራት ድርድር ሲያካሂዱ ቢቆዩም፣ ባለፈው ሰኔ ወር በኢራን እና በእስራኤል መካከል የተነሳውና 12 ቀናት የፈጀው ጦርነት ሂደቱን እንዳስተጓጎለው ተገልጿል::
ዩናይትድ ስቴትስ በጦርነቱ ወቅት የኢራንን የኒውክሌር ማዕከላት በሃይል በመምታት ጣልቃ መግባቷን ተከትሎ፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት እጅግ ተካሯል:: ኢራን በምክር ቤቱ ባቀረበችው ክስ አሜሪካ የሉዓላዊነት ጥሰት ፈጽማለች ስትል፣ ዋሽንግተን በበኩሏ የኢራን የኒውክሌር እንቅስቃሴ ለዓለም ደህንነት ስጋት መሆኑን ደጋግማ ገልጻለች::
ይህ በሰኔ ወር የተካሄደው ጦርነት ከመከሰቱ በፊት ሀገራቱ አምስት ዙር የኒውክሌር ውይይቶችን አድርገው የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን ድርድሩ ሙሉ በሙሉ መቋረጡንና ወደ ግጭት መሸጋገሩን የዲፕሎማሲ ምንጮች ጠቁመዋል::
ምላሽ ይስጡ