ሕዳር 16 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) ኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደሮች በኢትዮጵያ፣ ድርጅቱን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የብራንድ አምባሳደር አድርጎ አርቲስት አለማየሁ ታደሰን መሰየሙን አስታውቋል።
ይህ ሹመት ድርጅቱ ህዝባዊ መገኘቱን ለማጠናከር፣ የማህበረሰቡን ተሳትፎ ለማጎልበት እና በመላው ኢትዮጵያ ያሉ ህጻናትንና ወጣቶችን የመጠበቅና የማብቃት ተልዕኮውን ለማስፋት በሚያደርገው ጥረት ትልቅ ምዕራፍ ነው ተብሏል።
ድርጅቱ ይህን እርምጃ ለመውሰድ የወሰነው የፕሮግራሞቹን ስፋት እያሰፋና የአገር ውስጥ ሃብት የማሰባሰብ ጥረቱን እያጠናከረ ባለበት ወቅት ነው።
አላማውም ብዙ ማህበረሰቦችን ማዳረስ፣ ሰፊ ተሳትፎን ማነሳሳት እና ዘላቂነት ያለው ድጋፍን ማረጋገጥ ነው ተብሏል።
ኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደሮች፣ ተልዕኮውን የሚያጎላ፣ የህጻናትን መብት የሚያስከብር እና በባለድርሻ አካላት መካከል መተማመንን የሚፈጥር በጎ ተጽእኖ ፈጣሪ አካል እንደሚያስፈልገው ገልጿል።
የብራንድ አምባሳደሩም የገንዘብ ማሰባሰብ ጥረቶችን ለማጎልበት፣ አደረጃጀታዊ አጋርነትን ለማስፋት እንዲሁም በቂ የወላጅ እንክብካቤ ያጡ ህጻናት እና ወጣቶች የህዝብ ትኩረት እንዲያገኙ ለማስቻል ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተመላክቷል።
አርቲስት አለማየሁ ታደሰ በአቋማቸው፣ ለረጅም ጊዜ በዘለቀው መልካም ስማቸው፣ ለህጻናት ደህንነት ባላቸው ቁርጠኝነት እና ከድርጅቱ ተልዕኮ ጋር የሚጣጣም ስብእና ያላቸው ሆነው በመገኘታቸው ለዚህ ሚና መመረጣቸው ተመላክቷል።
አርቲስት አለማየሁ ፤ “የብራንድ አምባሳደር መሆን ከማዕረግ በላይ የሆነ እና ትክክለኛ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ለማበርከት የሚያበቃ ትልቅ ሃላፊነት እና እድል ነው፡፡ ባገኘሁት መድረክ ሁሉ ድምፄን ለማሰማትና የድርጅቱን ተልዕኮ ለማጉላት ሙሉ ቁርጠኝነቴን ስገልጽ ክብር ይሰማኛል” ብለዋል።
የኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደሮች በኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ብሄራዊ ዳይሬክተር አቶ ሣህለማርያም አበበ፣ አጋርነቱን አስመልክቶ ሲናገሩ፥ “ይህ አጋርነት የህጻናትን እና የወጣቶችን ድምጽ ወደ ፊት የማምጣት፣ የህብረተሰቡን ተሳትፎ የማነሳሳት እና ከለጋሾች፣ ከተቋማት እና ከተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የሚደረገውን ድጋፍ የማጠናከር አላማን ያገናዘበ ነው” ብለዋል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63 (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ