ሕዳር 18 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) በጂንካ ከተማ የተስተዋለውን የማርቨርግ ቫይረስን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ የቅድመ መከላከል ስራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡ ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ማዕከልና የብሔራዊ ህብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል በጋራ በመሆን በከተማዋ የተላላፊ በሽታ ልየታ መጀመሩን የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሃይሉ ተናግረዋል፡፡
በመዲናዋ በሚገኙ በሁሉም የጤና ተቋማት የቅኝት ልየታ ስራዎች መጀመራቸውን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ምልክቶቹ ከተለመዱ የጤና እክሎች ጋር ተቀራራቢ በመሆናቸው ማህበረሰቡ አጠራጣሪ ነገር ሲመለከት ባቅራቢያው ወዳለ የጤና ተቋማት ሊያመሩ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በጂንካ ከተማ ቫይረሱ ከተስተዋለበት ህዳር 5 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ለ38ሺህ 653 ሰዎች የልየታ ምርመራ መደረጉን ዶከተር መሳይ አንስተው፤ በአየር ማረፊያዎች፣ በድንበር ቦታዎች እና በሌሎች የመግቢያ እና የመውጫ ቦታዎች ላይም ምርመራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በየኬላዎች የሚደረገውን ቁጥጥር የማጠናከር፣ የቅኝት ሥራዎችን የማስፋትና ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ ትኩረት መደረጉን ዳይሬክተሩ አንስተው፤ በበሽታው ህይታቸው ያለፉ ሰዎች ቤተሰቦች ሁኔታውን በመቀበል በሽታው እንዳይስፋፋ ብሄራዊ የቀብር ቡድኑ ስርዓተ ቀብሩን እንዲያከናውን ማገዝ እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
አዲስ የሚያዙ ሰዎች ከተገኙ የለይቶ ማቆያ ማዕከላት፣ የሕክምና አቅርቦቶች እና የሰለጠኑ ሰራተኞች ዝግጁ መሆናቸውን ያረጋገጡት የኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ፤ ቫይረሱ ባልተገኘባቸው ክልሎችም ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ማሕበረሰቡ ከጤና ሚኒስቴር የሚሰጡ የጥንቃቄ መልእክቶችን በመተግበርና ጥቆማዎችን በ8335 እንዲሁም 952 ነፃ የስልክ መስመሮች ጥቆማ በመስጠት ሃላፊነቱን እንዲወጣ ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63 (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ