ሕዳር 17 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የመንገድ ላይ አደጋዎችን ለመቀነስ ወሳኝ እርምጃ ነው የተባለ ሲሆን፣ ጥራት እና ደረጃ የወጣላቸው የፍጥነት መቆጣጠሪያዎች፣ የደህንነት ምርቶች እና ግብዓቶች በአገር አቀፍ ደረጃ በይፋ ወደ ሥራ እንዲገቡ እና በአስገዳጅነት መጠቀም እንደሚጀመር ተገልጿል።
የመንገድ ደህንነት እና መድን ፈንድ አገልግሎት እና ሌሎች ስድስት ተቋማት ለአንድ ዓመት በምርቶቹ ጥራት ላይ ሲሰሩ መቆየታቸውን የአገልግሎቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ ሐሰን ገልጸዋል።
ከዛሬ ጀምሮ እያንዳንዱ ተቆጣጣሪ አካል እነዚህን ደረጃ የወጣላቸው የደህንነት ምርቶች እንዲጠቀሙ የሚያስገድድና እርምጃ የሚወስድ ይሆናል ተብሏል።
ይህ አሰራር የተጀመረው ከጥራት በታች የሆኑ እና ደረጃ ያልወጣላቸው የደህንነት መጠበቂያ ምርቶችን መጠቀም ለማስቆም በፌዴራል ከፍተኛ ተቋማት ቅንጅት እንደሆነ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ አቶ በርኦ ሐሰን አስረድተዋል።
ሚኒስቴሩ በየዓመቱ ከ3,000 በላይ ሰዎችን ሕይወት የሚቀጥፈውን እና 4 ቢሊየን ብር የሚገመት የኢኮኖሚ ኪሳራ የሚያስከትለውን የመንገድ አደጋ ለመቀነስ፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና በትምህርት ስረዓት በመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ በትምህርት ቤቶች ጭምር የመንገድ ደህንነት ትምህርቶች መሰጠት መጀመሩንም አክለዋል።
የመንገድ አደጋዎች ዋና ዋና ምክንያቶች እንደ ብቃትና ሥነ-ምግባር የጎደለው የአሽከርካሪ ስልጠና፣ የተሽከርካሪ ደህንነት ችግሮች ፤ የሕግ ተገዢነት እና ሥርዓት አልበኝነት መሆናቸውን አቶ በርኦ ጠቁመዋል።
የመንገድ ደህንነትን በተመለከተ በሚሰሩ ስራዎች ላይ ተሸከርካሪዎች ከአምስት አመት በላይ አገልግሎት እንዳይሰጡ ማድረግ ላይ መስራት እንደሚገባ ይህም አለም አቀፍ ደረጃ መሆኑም ተገልጻል፡፡
በይፋ የተጀመረው አስገዳጅ የደህንነት ሥራ ለቀላልና መካከለኛ እንዲሁም ለከባድ ተሽከርካሪዎች የመንገድ ደህንነት ተብሎ በሁለት የተከፈለ ነው የተባለ ሲሆን፤ በተጨማሪም የመመርመሪያ ተቋማት ደረጃ ወጥቶላቸው የመመርመሪያ መሳሪያዎች የተሻሻሉ ሲሆን፣ ባህላዊ የምዝገባ የመመርመሪያ ክፍተቶችን ለመሙላት በዲጂታል መንገድ የሚሰራ የተቀናጀ የደህንነት መሳሪያዎች ምርመራ ሥርዓት መዘርጋቱ ከጊዜ ቁጠባና ከደህንነት አንፃር ጠቃሚ መሆኑ ተገልጿል።
ይህ የተሽከርካሪ ደህንነት መመርመሪያ ዲጂታል አሰራር መረጃዎችን ከመመዝገብ ባሻገር በፍጥነት የሚመለከታቸውን አካላት በማስተሳሰር መረጃውን የሚያጋራ ሲሆን፣ ከመረጃ መጭበርበር፣ ከሐሰተኛ ማስረጃዎች እና ከትክክለኛነት አንፃር ከፍተኛ ጥበቃ ስላለው ፈጣንና ራሱን የቻለ አሰራር ነው ተብሏል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63 (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ