ሕዳር 15 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የስደተኞችና ከስደት ተመላሽ አገልግሎት የዩኤስ ኤድ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ መቋረጡን ተከትሎ ለስደተኞቹ መቅረበ ከሚገባው ምግብ ውስጥ 40 በመቶ ብቻ እየቀረበላቸው መሆኑን የሩብ አመት አፈፀፀሙን ለውጭ ግንኙነትና ሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ባቀረበበት ወቅት አስታውቋል፡፡
የተቋማቸውን የሩብ አመት አፈፃፀም ያቀረቡት የአገልግሎቱ ዋና ዳሬክተር – ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ክልሎች ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ተጠልለው እንደሚገኙ በማመላከት ከእነዚህም ውስጥ በጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን የመጡ ከ4 መቶ ሺህ በላይ ስደተኞች እንደሚገኙና ካሉ ስደተኞች ውስጥ የደቡብ ሱዳን ሰደተኞች ከፍተኛውን ቁጥር መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡
ለስደተኞች የሚቀርበዉን የምግብ አቅርቦት በተመለከተ ከዚህ ቀደም መቅረብ ከነበረበት 65 በመቶ ብቻ የሚቀርብ እንደነበርና አሁን ደግሞ ቁጥሩ አሽቆልቁሎ 40 በመቶ መድረሱን አብራርተዋል፡፡ ዩኤስ ኤድ ድጋፉን ማቆሙን ተከትሎ አሁን ላይ ስደተኞቹ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸዉን አስታዉቀዋል፡፡
በተለይም ከስደተኞች ድጋፍ ጋር በተገናኘ የሌሎች ሀገራት ተሳትፎ እምብዛም በመሆኑ፤ ችግሩን በይበልጥ እንዳባባሰው ጠቅሰዉ ተቋማቸው ሌሎች ምንጮችን በአማራጭ ለመጠቀም ማቀዱንም አመላክተዋል፡፡ አሁን ላይ ስደተኞችን ተቀብለው እያስተናገዱ ላሉ ክልሎችም ድጋፎች እየተደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የውጭ ግንኙነትና ሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በበኩሉ በቀጣይ ተቋሙ ያሉ ችግሮችን በሚገባ በማሳወቅ ድጋፍ የሚያገኝባቸውን አማራጮች መከተል እንደሚገባዉ አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡
ምላሽ ይስጡ