ሕዳር 10 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ)በገንዘብ እጥረት እና በአካባቢው ባለው ውጥረት ምክንያት የትግራይ ክልል የኩላሊት ሕመምተኞች ከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸውን የኩላሊት ሕመምተኞች ማኅበር ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል።
በገንዘብ እጥረት ምክንያት በርካታ ታካሚዎች ሕክምናቸውን እያቋረጡ እንደሆነ የሚናገሩት የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሃፍቶም አባዲ፣ በኩላሊት ማጠቢያ ማሽን ብልሽት ምክንያት ተደጋጋሚ ችግር ውስጥ እየወደቁ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ባለው ተደጋጋሚ ውጥረት ምክንያት ታካሚዎች ላልተገባ የኢኮኖሚ ችግር ከመጋለጣቸውም በላይ ሕክምናቸው እየተቋረጠ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።
ከዚህ ቀደም ማኅበሩ መድኃኒትና መሰል የሕክምና መሣሪያዎችን ከአዲስ አበባ ይወስድ የነበረ ቢሆንም፣ ከአይደር ሆስፒታል ጋር በመነጋገር ሆስፒታሉ ሲያቀርብ መቆየቱንና አሁን ላይ ግን ሆስፒታሉ ግብዓት ማቅረብ እንዳቆመ ገልጸዋል።
በክልሉ አሁን ላይ ሰባት የኩላሊት ማጠቢያ ማሽን ብቻ እንደሚሠራና ወረፋ እንደበዛበት የተናገሩት አቶ ሃፍቶም፤ የክልሉ ጤና ቢሮ ለታካሚዎች ድጋፍ እንዲያደርግ በተደጋጋሚ ማኅበሩ ቢጠይቅም ቢሮው ምላሽ እንዳልሰጣቸው ተናግረዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ አለመሆኑን ሥራ አስኪያጁ በመግለጽ፣ በክልሉ የሚገኙ የኩላሊት ታካሚዎች ለከፍተኛ እንግልት፣ አልፎ ተርፎም ለሕልፈት እየተዳረጉ መሆኑን አስታውቀዋል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63 (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ