በአለም አቀፉ የስኳር ፌድሬሽን የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የስኳር ህመም እንዳለባቸውና በዚህም ከአጠቃላይ ህዝቡ 3.3 በመቶ የሚሆነው ለበሽታው ተጋላጭ መሆኑን ነው። የስኳር ህመም ቀድሞ ምልክት የማያሳይ በመሆኑ በኢትዮጵያ በየጊዜው በህመሙ ከሚጠቁት ሰዎች 67 በመቶዎቹ ህመሙ እንዳለባቸው እንኳን እንደማያውቁ ጥናቱ አሳይቷል፡፡
በዓለም ዙሪያም 50 በመቶ ተጠቂዎች ህመሙ እንዳለባቸው እንደማያውቁ የገለጸው ጥናቱ ፤ በአፍሪካ ደግሞ ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑ ህመሙ ያለባቸው ሰዎች በህመሙ አንደተጠቁ አያውቁም ይላል ። በስኳር ህመም ከተጠቁ 653 ሚሊዮን ሰዎች 80 በመቶዎቹ ኢትዮጵያ በምትመደብበት በማደግ ላይ ባሉ ሃገራት የሚኖሩ መሆናቸውን ያስቀምጣል፡፡ በሃገራችን በየአመቱ ህዳር ወር ላይ በልዩ ሁኔታ የሚከበረው የአለም የስኳር ህሙማንን ቀን በማስመልከት አጠቃላይ ከህመሙ ጋር በተያያዘ በዳሰሳ ጥንቅራችን ልንመለከተው ወደናል ።
በአለም አቀፍ ደረጃ የስኳር ህመም በከፍተኛ ደደጃ እየጨመረ እንደመጣ በጥናት መረጋገጡን የገለጹት ዶ/ር አዜብ ለሊሳ ፤ በቅርቡ በተጠኑ ጥናቶች በአለማችን 589 ሚሊየን የሚሆኑ ከ20 እስከ 39 የድሜ ክልል ያሉ ወጣቶች ከስኳር ህመም ጋር ይኖራሉ ብለዋል። በአብዛኛው በ አይነት 2 የስኳር አይነት የተያዙ መሆናቸውን ተናግረው ፤ ይህም የአኗኗር ሁኔታችን ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ያብራራሉ።
የከተማ መስፋፋት ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በበቂ ሁኔታ ባለማድረግ ና በመሳሰሉት ምክኒያቶች ከ 9 ሰው አንድ ሰው በስኳር ህመም ይጠቃል ሲሉም ተናግረዋል ። አሁን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ያለው የስኳር ህመም በዋናነት በማደግ ላይ ባሉ ሃገራት መሆኑን ተናግረው ፤ በሃገራችንም አሳሳቢ የህመም አይነት ነው ብለዋል።
በተለይም በፋብሪካ የተቀነባበሩና ታሽገው ለገበያ የሚቀርቡ ምግቦች አጠቃቀም አሁን ላይ በሃገራችን በከፍተኛ ሁኔታ ቁጥሩ እየጨመረ ላለው የስኳር ህመም መነሻ መክኒያት ነው የሚሉት ዶ/ር አዜብ ፤ ታሽገው ለገበያ የሚቀርቡት ምግቦች የስኳር ፤ የጨውና የስብ መጠናቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል ። የታሸጉ መግቦችን አዘውትሮ ከመጠቀም አኳያ በከተማ ያለው የስኳር በሽታ ስርጭት ከፍተኛ ቢሆንም በገጠሩ ክፍል ያለው የስኳር ታማሚ ቁጥር ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ያስረዳሉ።
ሌላኛው በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የውስጥ ደዌና የስኳር ሆርሞኖች ህክምና እስፔሻሊስት ዶ/ር ቴድሮስ አበራ ፤ አጠቃላይ በህብረተሰቡ ላይ ያለው የግንዛቤ ክፍተት ታማሚው ላይ ፍርሃትንና በሽታውን አምኖ መቀበል ላይ ከፍተኛ የሆነ ስነ-ልቡናዊ ጫናን እያሳደረ እንደሚገኝ አብራርተዋል ። እንደሃገር ያለው የህክምና ስራት መሻሻሎች ያሉት ቢሆንም እንደ ስኳር ያሉ ህክምናዎች ላይ የባለሙያዎች እጥረት እንዳለ ያነሳሉ ። ከበሽታው መስፋፋትና ከታካሚው ቁጥር መጨመር አንጻር በስኳር ህመም እስፔሻላይዝ ያደረጉ ሃኪሞች ላይ እጥረቶች መኖራቸውን ገልጸዋል ።
በሌላ በኩል ከስኳር ህመሞች ጋር በተያያዘ የሚመጡ በሽታዎች ላይ በየተቋማቱ የሚደረጉ እንደ ኮሊስትሮል ፣ ልብ እና የግፊት መጠን ያሉ ዋና ዋና ምርመራዎች እንደሚደረጉ ተናግረው ከዛ በተጨማሪ ሊደረጉ የሚገቡና አስፈላጊ የሆኑ እንደ አይን ምርመራና የእግር ምርመራዎች እንደማይደረጉ የሚገልጹት ዶ/ር ቴድሮስ በአጠቃላይ የህክምና ተደራሽነትና የግብዓት እጥረት እንደሃገር መኖሩን ገልጸው ፤ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ያለውን ክፍተት ለመሙላት ስራዎችን እየሰሩ ቢሆንም ከፍተቶች በስፋት እንደሚስተዋሉ አመላክተዋል ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የስኳር ህመም መድሃኒትም ሆነ ኢንሱሊን በከተማዋ ባሉ የመድሃኒት መደብርም ሆነ በመንግስት ተቋማት ማግኘት እንዳልቻሉ ብዙ ታካሚዎች ሲናገሩ ይደመጣል ። መናኸሪያ ሬድዮ ያነጋገራቸው ከስኳር ህመም ጋር ለረጅም አመት የኖሩት ወ/ሮ ብርቱካን እንደገለጹት ፤ በህክምና አሰጣጡና በመድሃኒት አቅርቦቱ ዙሪያ በርካታ ችግሮች እንደሚያጋጥሟቸው ተናግረዋል ።
በተለይም በመንግስት የህክምና ተቋማት ሃኪሞች የሚያዙትን ያክል መድሃኒት በጤና መድህን አማካኝነት በመድሃኒት መደብሮች ማግኘት የማይቻልበት አጋጣሚ በብዛት እንዳለና በግል የመድሃኒት መደብር በእጥፍ ዋጋ ለመግዛት እንደሚገደዱ ተናግረው በዚህም የሚደርሱ በርካታ መጉላላቶች እንዳሉ ገልጸዋል።
በስኳር ህመም ሳቢያ ሌሎች ተጨማሪ ህመሞች የሚከሰቱ በመሆናቸው በባዶ ሆድ ለቅድመ ምርመራ ሲኬድ መሳሪያ የለም ወይም አይሰራም በሚል መጉላላቶች እንደሚያጋጥሙ የገለጹት ወ/ሮ ብርቱካን፤ ለህሙማኑ በልዩ ሁኔታ የተሰጠ ትኩረት አለመኖሩን ይገልጻሉ ። የመድሃኒት አቅርቦት ላይ ካሉ ክፍተቶች በተጨማሪ በጤና መድህኑ ላይ የተደረገው ያልተገባ ጭማሪ ሌላኛው ተግዳሮት እንደሆነባቸው ገልጸው ፤የመድሃኒት አቅርቦቱ ባልተሻሻለበት ሁኔታ የጤና መድህኑ ላይ ከፍ ያለ ክፍያ መጠየቁ አግባብነት የለውም በለዋል።
ሌላኛዋ የስኳር ታማሚና የስነልቡና ባለሙያዋ ንያት ዮሃንስ፤ ከስኳር ህመም ጋር በተያያዘ እንፍደሃገር ያለው የግንዛቤ ክፍተት ከፍተኛ መሆኑን ይገልጻሉ። በተለይም በታማሚው ቤተሰብ በኩል ከአመጋገብና በነጻነት ከመንቀሳቀስ ጋር በተያያዘ ያለው ግምትና አመለካከት ደካማ በመሆኑ ለስኳር ታማሚው የሚፈጥረው የስነልቡና ጫና ከፍተኛ ነው ይላሉ።
በተጨማሪም በህክምና አሰጣጡ ላይ ታማሚው የሚከተለውን የአመጋገብ ስራት እንዲያስተካክል ከመምከርና መድሃኒቱን በአግባቡ እንዲወስድ ከማሳሰብ ባለፈ ስነ-ልቡናዊ ድጋፍ እንደማይደረግ ተናግረው፤ በዚህም ህሙማኑ ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚፈጠር ገልጸዋል ። ለህብረተሰቡ ስለበሽታው ግንዛቤ ከመስጠትም ባለፈ የጤና ባለሙያውም በራሱ ለታካሚው የስነልቡና ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በ1976 ከ 40 አመት በፊት የተመሰረተው የኢትዮጵያ ስኳር ሕሙማን ማኅበር ከስኳር ሕመም ጋር ለሚኖሩ ሰዎች መረጃ ማቅረብና እንዲያገኙ የማስቻል፣ ከሕክምና አቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮችን መፍታትና ሕሙማኑ ስለ በሽታውና የሚገጥማቸውን ችግር በሚመለከት መወያየት የሚያስችላቸውን መድረክ የማዘጋጀት፣ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት የማህበሩ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ኤርሚያስ ገ/ማሪያም፤
ከስኳር ህመም ጋር ለሚኖሩ የማህበሩ አባላት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረው አሁን ላይ 96 ቅርንጫፎችን በክልል ከተሞች በመክፈት እየሰራ ነው ብለዋል። በውጪ ከሚኖሩ የእርዳታ ተቋማትጋር በመነጋገር ከ18ሺ በላይ ለሆኑ በኢትዮጵያ ለሚኖሩና እድሜያቸው ከ 25 አመት በታች ለሚሆኑ ህጻናትና ታዳጊዎች የአይነት አንድ የስኳር ህሙማን በሙሉ የመድሃኒትና ጠቃሚ መሳሪያዎች ደጋፍ ያለምንም ክፍያ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል። አንዳንድ አከባቢዎች ላይ ያለው የሰላም ሁኔታ ፣ ከውጪ መድሃኒቶቹ ሲገቡ የማጓጓዣ ወጪን ጨምሮ ለመድኃኒቱ ማስቀመጫ ማቀዝቀዣዎች ክፍያ በየጊዜው መጨመር በስራው ሂደት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች መሆናቸውን አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አወል ሃሰን ፤ አሁን ላይ የስኳር መ4ድሃኒት የስርጭት መጠን ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ መሆኑን ተናግረው፤ በሩብ አመቱ 1.2ሚሊየን የስኳር መድሃኒቶች በሁሉም ቅርንጫፎች በማከፋፈል በመላው ሃገሪቱ ተደራሽ መደረጉን ገልጸዋል።
የመድሃኒት ስርጭቱን ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ በመንግስት ድጎማ አማካኝነት እየቀረበ እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ከጤና ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ለህሙማኑ እየተሰራ መሆኑን ተናግረው፤ በክምችት ከፍሉ በቂ የሆነ የመድሃኒት ክምችት መኖሩን ገልጸው፤ በሃገሪቱ የመድሃኒት እጥረት አለ የሚሉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
በጤና ሚኒስቴር በበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሙሴ ገ/ሚካኤል፤ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እንደሃገር ካላቸው ከፍተኛ ጫና አንጻር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የህክምና የባለሙያዎች ስልጠና መመሪያ መዘጋጀቱንና ከ1ሺ በላይ ለሆኑ የጤና ተቋማት የባለሙያ ስልጠናዎች ሲሰጡ መቆየታቸውንና በዚህም የህክምና ባለሙያ እጥረቱን ለማስቀረት ወደ መሰረታዊ የጤና ተቋማት ወርዶ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን መሰራቱን አብራርተዋል።
ከግንዛቤ ማስጨበጥ ጋር በተያያዘ ከ30ሺ በላይ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችም ስልጠና እንደተሰጣቸው ተናግረው፤ የአይነት የስኳር በሽታን በመሰረታዊ የጤና ተቋማት እንዲሰጥ መደረጉን ጠቅሰው የጤና ስራቱን ለማስፋፋትና ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከስኳር ህመም መድሃኒት ጋር በተያያዘ ያለውን የአቅርቦት ችግር ለፍታት ከመድሃኒት አቅራቢ ና ከስቋር ህሙማን ማህበር ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው አቅርቦትሩ ላይ መሻሻሎች እየታዩ እንዳለ አመላክተዋል።
ለስኳር ህመም አጋላጭ ከሆኑት ምክኒያቶች አንዱ የሆኑት የታሸጉና ጤናማ ያልሆኑ መግቦች መሆናቸውን ተከትሎ ቁጥጥር ለማድረግ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ታክስ መጨመሩንና ለመቆጣጠር የሚያስችል አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው ረቂቁላይ ውይይቶች ተደርገው ወደ ፍትህ ሚኒስቴር ሊላክ መሆኑንና አዋጁ ሲጸድቅ በቀጥታ ለመቆጣጠር የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።
አሁን ላይን በአለም አቀፍ ደረጃ የስኳር ህሙማን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች ገልጸዋል። በተለይም በማደግ ላይ ያሉ ሃገራት በከፍተኛ ደረጃ የታሸጉ መግቦች አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በሽታው እየተስፋፋ መሆኑም ተነስቷል። ስለበሽታው እንደሃገር ያለው የግንዛቤ ደረጃ ላይ ሊሰራ እንደሚገባና ከመድሃኒት አቅርቦትና ከህክምና አሰጣትና ተደራሽነት ጋር በተያያዘ ያሉ ክፍተቶች ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ያነጋገርናቸው አካላት ያሳፈሩት ሃሳብ ነው።
በአስናቀች መላኩ
ምላሽ ይስጡ