ሕዳር 04 ቀን 2018 (መናኸሪያ ሬዲዮ) ሞሮኮ ለዓለም ዋንጫ ዝግጅት በሺዎች የሚቆጠሩ ውሾችን በመንገድ ላይ በመግደል መከሰሷም ተሰምቷል።
የ2030 የዓለም ዋንጫን በጣምራ ከፖርቹጋል እና ስፔን ጋር የማሰናዳት ወርቃማ እድል ያገኘችው ሞሮኮ ጋር በተያያዘ አስደንጋጭ ዘገባዎች እየወጡ ሲሆን፣ ሀገሪቱ ለዓለም ዋንጫው ከተማዎቿን “ለጎብኚዎች ለማጽዳት” በሚል ሽፋን በሺዎች የሚቆጠሩ ባለቤት የሌላቸውን (የመንገድ) ውሾች በጅምላ እየገደለች እንደሆነ ተዘግቧል።
የእንስሳት መብት ተሟጋቾች እንደገለጹት፣ ሞሮኮ ወደ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ ውሾችን እስከ 2030 ዓ.ም ድረስ የማጥፋት ዕቅድ እንዳላት የተገለፀ ሲሆን ይህም ዓለም አቀፍ ቁጣን አስነስቷል።
በዘገባዎቹ መሠረት፣ ባለሥልጣናት ውሾቹን ለመግደል እየተጠቀሙባቸው ያሉት ዘዴዎች አሰቃቂ ሲሆኑ፣ እነዚህም በከፍተኛ መርዛማነት በሚታወቀው ስትሪክኒን (strychnine) መርዝ መግደል፣ በአደባባይ በሽጉጥ መምታት፣ እንዲሁም አንዳንዶቹን ደግሞ በሕይወት እያሉ ወደ ጅምላ መቃብር መጣልን ይጨምራል ተብሏል።
የእንስሳት መብት ተሟጋች ድርጅቶች ይህንን የሞሮኮ የጅምላ ግድያ አፀያፊ እና አስከፊ ሲሉ አውግዘዋል። እንደ ጄን ጉድል ያሉ ታዋቂ ሰዎች ሳይቀር የአለም አቀፉ እግርኳስ አወዳዳሪው አካል ፊፋ በዚህ ጉዳይ ላይ ጣልቃ እንዲገባ እና ግድያው እንዲቆም ግፊት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት፣ የሞሮኮ ባለሥልጣናት ክሱን መሠረተ ቢስ ነው ሲሉ ውድቅ ቢያደርጉም፣ የእንስሳት መብት ተሟጋቾች ግን ምርመራ እንዲደረግበት እና ተፈጥሮአዊ እና ሰብዓዊ በሆነ መንገድ የውሾችን ቁጥር ለመቆጣጠር የሚያስችል ዘዴ ለምሳሌ ውሾችን መያዝ እና ተያያዥ ጉዳዮች እንዲተገበሩ አጥብቀው እየጠየቁ ይገኛሉ።
እነዚህ የጅምላ ግድያዎች በልጆችና በማህበረሰቡ ላይ የስነ-ልቦና ጉዳት እያደረሱ እንደሆነ እና ይህ ድርጊት ሞሮኮ የገባችውን የእንስሳት ደህንነት ጥበቃ ቃል የጣሰ ነው በማለት ተቃውሞ ቀርቧል።
ይህ ዘገባ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን እና የእንስሳት መብት ተሟጋች ድርጅቶች የወጣ መረጃ ነው፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63 (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ