ሕዳር 04 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የመጀመሪያው የኢትዮ-ባንግላዲሽ የንግድ ሾው በአዲስ አበባ መካሄዱ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የንግድ ትስስር ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ እስያና ፓሲፊክ ሀገራት አምባሳደር ደዋኖ ከድር ገለጹ። አምባሳደሩ ይህን የተናገሩት በአፍሪካ-ባንግላዲሽ ንግድ ሾው እና ቢዝነስ ሰሚት መርሃ ግብር ላይ ነው።
አምባሳደር ደዋኖ እንዳሉት፣ ባንግላዲሽ እንደ ሀገር ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ጋር ለመስራት ትፈልጋለች፤ ከእነዚህም መካከል ኢትዮጵያ አንዷ የመዳረሻ ሀገራቸው እንድትሆን ይፈልጋሉ። ሀገሪቱ በጨርቃጨርቅ፣ በቆዳ፣ በመድኃኒትና በቴክኖሎጂ ምርቶች የምትታወቅ በመሆኗ፣ ኢትዮጵያ ከእርሷ ጋር የገበያ ትስስር ብትፈጥር ተጠቃሚ እንደምትሆን ይገመታል።
ምንም እንኳን ከባንግላዲሽ ጋር የረጅም ጊዜ ግንኙነት ታሪክ ባይኖርም፣ ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ምርት ለውጭ ከሚያቀርቡ ሀገራት ተርታ ውስጥ በመሆኗ ኢትዮጵያ የምትጠቀምበት የንግድ ሂደት ይኖራል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በተለይ ጥጥ እና የጥጥ ምርቶችን እንዲሁም ቡናን ወደ ባንግላዲሽ ለመላክ ሰፊ አቅም እንዳላት አምባሳደር ደዋኖ ጠቅሰዋል። በተጨማሪም፣ በባንግላዲሽ በኩል ከአምስት ያላነሱ ተቋማት አስቀድመው በኢትዮጵያ ሥራ መጀመራቸውና የቆንስላ ጽሕፈት ቤታቸውም መልካም የዲፕሎማሲ ሥራ ላይ መገኘቱ አመቺ የንግድ ትስስር ለመፍጠር አጋዥ መሆኑን አብራርተዋል።
በኢትዮ-ባንግላዲሽ የመጀመሪያ የንግድ ሾው ላይ 38 ያህል የባንግላዲሽ ተሳታፊ ቡድን መገኘቱን የገለጹት አምባሳደር ደዋኖ፣ ወደፊት ፍላጎቶች እየተለዩ ግንኙነቱ እንዲጠናከር ከቆንስላ ጽሕፈት ቤታቸው ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል።
በመጨረሻም፣ ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ጋር በንግድና መሰል ጉዳዮች ላይ የምትፈጥራቸው ግንኙነቶች የገበያ መዳረሻዎቿን ከማስፋፋት አንጻር የላቀ ሚና እንዳላቸው በኢትዮ-ባንግላዲሽ የንግድ ሾው ሰሚት ላይ ተመላክቷል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63 (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ