ህዳር 01 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት የሚቀጥፍ፣ ብዙሃኑን ለመፈናቀልና ለጥቃት የሚዳርገውን ጦርነት ማስቆም የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን የሀገር ሽማግሌ እና የሰላም ሴቶች ሕብረት ለጣቢያችን ገልጸዋል።
የሀገር ሽማግሌው ፕሮፌሰር አህመድ ዘኸሪያ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የሚታየው የእርስ በእርስ ግጭቶች ወደ ጦርነት እንዳያመራ መንግሥት ማንኛውንም የሰላም እርምጃ ሊወስድ ይገባል ሲሉ ገልፀዋል።
“በታሪካችን ከጦርነት ያተረፍነው የሌለ ከመሆኑም በላይ ለሌሎች የኢትዮጵያን መረጋጋት ለማይፈልጉ አካላት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በሀገራችን ጦርነት እንዲቀሰቀስ ማድረግአይገባም” ብለዋል።
ከምንጊዜውም በላይ ውስጣዊ አንድነት እና ሰላም የሚያስፈልግበት ጊዜ መሆኑን ገልጸው፣ እንደሀገር ከውጭ ወራሪዎች ራሳችንን ለመከላከል አንድነታችንን ማጠናከር ወሳኝ ነው ብለዋል። ለሁለንተናዊ የሀገር እድገት በዲፕሎማሲና ኢኮኖሚ መጠናከር አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑንም ፕሮፌሰር አህመድ አስታውቀዋል።
የሰላም ሴቶች ሕብረት አስተባባሪ ወይዘሮ መዓዛ በቀለ በበኩላቸው የግጭት እና ጦርነት አዝማሚያን በዘላቂነት ለመፍታት የሃይማኖት ተቋማት በሁሉም ቦታ እንዲሰሩ እያሳሰብን እንገኛለን ብለዋል።
ሕብረቱ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ ከእስልምና እምነት፤ ከካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እና ከሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት የተውጣጣ በመሆኑ፣ ሁሉም በየእምነቱ ስለሰላም መስበክ ብቻም ሳይሆን ሰላም እንዲሰፍን በጋራ የሚያስተባብሩትን ሥራ በቅርቡ እንደሚጀምሩ ጠቁመዋል።
ሀገር ከጦርነት ሳታገገም ዳግም ጦርነት ሊቀሰቀስ ስለማይገባው ሁሉም ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት፣ አለመግባባትንም በንግግር መፍታት እንደሚገባ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63 (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ