ህዳር 01 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)በግንቦት ወር ይካሔዳል በተባለው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ፤ ምርጫ ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታ ስለመኖሩ በዝርዝር ገምግሞ አቋሙን ይፋ እንደሚያደርግ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የተሰኘው የ5 ፓርቲዎች ቅንጅት ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታወቋል፡፡
መስከረም 10/2018 ዓ/ም 5 የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ በሚያደርጉ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የተሰኘ ቅንጅት መመስረታቸው ይታወሳል፡፡
ከዚህ ቀደም ስለሀገራዊ ምርጫው መካሄድ አለመካሄድ እርግጠኛ አለመሆናቸውን ገልጸው የነበሩት የቅንጅቱ ፕሬዝዳንትና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ሊቀ-መንበር አቶ አብርሀም ጌጡ፤ አሁንም ቢሆን ቅንጅቱ ነባራዊ ሀገራዊ ሁኔታውን በዝርዝር ገምግሞ አቋሙን እንደሚያንጸባርቅ ተናግረዋል፡፡
ሀገር አሁን ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ሰላማዊና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ ያስችላል ለማለት የሚያስደፍር አይደለም የሚሉት የቅንጅቱ ፕሬዝዳንት፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያሉ ግጭቶች አስቻይነቱን ጥያቄ ውስጥ ያስገባል ብለዋል፡፡
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በምርጫ ሂደቱ ስለመሳተፍ አለመሳተፍ ቅንጅቱ ውሳኔ ላይ አለመድረሱን ያስታወቁት አቶ አብርሃም፤ አምስቱም ፓርቲዎች በጋራ በመነጋገር እና ነባራዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን በዝርዝር በመግምግም አስቻይ ሁኔታ ካለ በምርጫው እንደሚሳተፉ አረጋግጠዋል፡፡
ፓርቲዎቹ በሰላማዊ ትግል እንደሚያምኑና ማንኛውም አካል በምርጫ ሂደት ህዝብ በሚሰጠው ድምፅና በውጤቱ ስልጣን መያዝ እንዲሁም ሀገር መምራት እንዳለበት የጋራ አቋም እንዳላቸው በአጽንዖት ተናግረዋል፡፡
ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ እናት ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና አማራ ጊዮናዊ ንቅናቄ በጋራ የመሰረቱት ቅንጅት እንደሆነ ይታወቃል፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63 (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ