ጥቅምት 25 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) – አርሰናል ብራይተንን፣ ክሪስታል ፓላስ ደግሞ ክዊንስ ፓርክ ሬንጀርስን በመርታት በካራባኦ ካፕ አራተኛ ዙር ጨዋታ እንዲገናኙ የዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓቱ ይፋ እንዳደረገው ይታወሳል። ታዲያ ከመርሐ ግብር መደራረብ ጋር በተያያዘ ለቡድኖቹ የተሰጠው እረፍት አንድ ቀን ብቻ መሆኑ ግርምትን ፈጥሯል።
የካራባኦ ዋንጫ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ የሆነው አርሰናል ከክሪስታል ፓላስ የሚያደርጉት ጨዋታ የፈረንጆቹ ማክሰኞ ታኅሣሥ 23 ላይ እንዲደረግ ተወስኗል።
ይህ ቀን የተወሰነው በዋነኝነት የክሪስታል ፓላስን የዩሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ተሳትፎ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነውም ተብሏል። ሁለቱም ክለቦች ከዚህ ቀደም እሁድ ታኅሣሥ 21 ዕለት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን እንደሚያደርጉ የፕሪሚየር ሊጉ መርሐ-ግብር ያሳያል።
አርሰናል በሜዳቸው ኤምሬትስ ስቴዲየም ከኤቨርተን ጋር ይጫወታሉ፤ ክሪስታል ፓላስ ደግሞ በሜዳቸው ሴልኸርስት ፓርክ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ይገናኛሉ።
በዚህም ምክንያት ቡድኖቹ ለካራባኦ ዋንጫው ጨዋታ የተሰጣቸው የእረፍት ጊዜ አንድ ቀን ብቻ ሆኗል። ይህም በሁለቱም ክለቦች አመራሮች ቁጣን የቀሰቀሰ ርዕስ ሆኗል። ሕጉንም የሚጥስ ነው። አንድ ክለብ ቢያንስ በ72 ሰዓታት እረፍት ውስጥ ነው ቀጣዩን ጨዋታ ማድረግ ያለበት። ይህ የአለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል (ፊፋ) ያወጣው ወይም የደነገገው ሕግ ቢሆንም፣ እንደአስፈላጊነት ሲታጠፍ ይታያል፤ ተደራራቢ መርሐ-ግብሮችም ካሉ ሕጉ ላይሠራ ይችላል። ከዚህ አንጻር ይህ የለንደን ደርቢ በተያዘለት ቀንና ሰዓት መከናወኑ የማይቀር ስለመሆኑ እየተገለጸ ይገኛል።
ሁለቱ ቡድኖች ዘንድሮ በፕሪሚየር ሊጉ በኤምሬትስ ስቴዲየም ያደረጉትን ጨዋታ ፓላስን ለቆ አርሰናልን የተቀላቀለው ኤብሬቺ ኤዜ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል አርሰናል 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት ጨዋታውን ማሸነፋቸው አይዘነጋም።
ሁለቱ ቡድኖች በቂ ዝግጅት ሳያደርጉ ይህን ጨዋታ ከእሁድ ታኅሣሥ 21 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ካከናወኑ በኋላ በአንድ ቀን እረፍት ብቻ ድጋሚ ለመጫወት ይገደዳሉ ማለት ነው።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
	
											
			
			
			
			
			
			
			
			
ምላሽ ይስጡ