ጥቅምት 21 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቅድመ ግንባታ እና በግንባታው ሒደት የነበሩ ፈተናዎች የተቀለበሱበት መንገድ፤ በድህረ ምረቃውም መቀጠል እንዳለበት የግድቡ ቴክኒካል ተደራዳሪዎች ተናግረዋል።
Harnessing the Nile: The GERD Experience in Development and Diplomacy በሚል ርዕስ አምባሳደር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለና ሌሎችም ተደራዳሪዎች በተገኙበት አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴክኖሎጂ እና ቢልት ኢንቫይሮመንታል ኮሌጅ በትላንትናው እለት የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል።
ከአንዳንድ የተፋሰሱ ሀገራትና አጋሮቻቸው ግድቡ እንዳይገነባ ፖለቲካዊና ቴክኒካዊ ሴራዎች ሲሰነዘሩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ የነበረው ዘርፈ ብዙ ፈተና በታለፈበት መልኩ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ አምባሳደር ስለሺ በቀለ በመድረኩ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያውያን አቅም የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብዙ መስዋትነት የተከፈለበት መሆኑን ያስታወሱት አምባሳደሩ በተለይ ከግብጽ ለሚሰነዘረው አሉታዊ ተጽዕኖ እንደ በፊቱ መካች የሆነ አቋም ይዞ መቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብን የገነባችበት መንገድ ሌሎች ሀገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ልምድ እንደሚሆን ሌላኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ቴክኒካል ተደራዳሪ ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው ተናግረዋል።
በግንባታው ሂደት የተሳተፉ አለም አቀፍ ባለሙያዎችና አማካሪዎች ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ያካፈሉት ሰፊ ልምድ መኖሩ በቀጣይም በራስ አቅም ለሚሰሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች የአሰራርና የእውቀት ልምድ የተቀሰመበት ነው ብለዋል።
በርካታ ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆኑ ብዙ የስራ ዘርፎች የተሳተፉበት በመሆኑ ልምዱ ሀገር ለምትወጥናቸው ሌሎች ፕሮጀክቶች ላቅ ያለ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።
አምባሳደር ስለሺ በቀለ እና ኢ/ር ጌዲዮን አስፋውን ጨምሮ ተደራዳሪ ፕሮፌሰር ይልማ ስለሺ እና ተደራዳሪ ዶ/ር በለጠ ብርሃኑም አዲስ አበባ ዩኒቨስርቲ 75ተኛ ዓመቱን አስመልክቶ ባሰናዳው ፕሮግራም ላይ ተገኝተዋል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ