ጥቅምት 17 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሁኑ ወቅት እያካሄዱ ባሉት የእስያ ጉብኝት ወቅት የሰሜን ኮሪያውን መሪ ኪም ጆንግ ኡንን ለመገናኘት ‘በጣም ፍላጎት’ እንዳላቸው ተናገሩ። ፕሬዝዳንቱ ይህ ስብሰባ እንዲሳካ ከተፈለገ በደቡብ ኮሪያ የሚያደርጉትን ቆይታ ለማራዘም ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከማሌዥያ ወደ ጃፓን በመብረር ላይ ሳሉ በአየር ኃይል አንድ አውሮፕላን ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ከሰሜን ኮሪያው መሪ ጋር “ታላቅ ግንኙነት” እንዳላቸው ጠቅሰው፣ “መገናኘት ከፈለገ እኔ ደቡብ ኮሪያ እሆናለሁ” ብለዋል።
ትራምፕ እና ኪም ጆንግ ኡን በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ሶስት ጊዜ ያህል የተገናኙ ሲሆን፣ የመጨረሻው ስብሰባቸው እ.ኤ.አ. በ2019 በሁለቱ ኮሪያዎች መለያያ መስመር (DMZ) ላይ ነበር።
ፕሬዝዳንቱ ሊደረግ በሚችል ስብሰባ ላይ ምን ሊያቀርቡ እንደሚችሉ ተጠይቀው፣ በሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች የውይይት መጀመሪያ ሊሆኑ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል።
ከዚህ ቀደም ሰሜን ኮሪያ አዲስ ድርድር ልትጀምር እንደምትችል የገለጸች ቢሆንም፣ ዋሽንግተን የሀገሪቱን የኑክሌር አቅም “የማይቀለበስ” አድርጋ እንድትቀበል ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጧ ይታወቃል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጃፓንን ተከትሎ ወደ ደቡብ ኮሪያ በማቅናት ከደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ሊ ጄ ማይዩንግ ጋር የሚወያዩ ሲሆን፣ በተጨማሪም በእስያ-ፓሲፊክ የኢኮኖሚ ትብብር (APEC) ጉባኤ ላይ ይሳተፋሉ። ቢሆንም፣ በጉብኝቱ መርሃ ግብር ውስጥ ከኪም ጆንግ ኡን ጋር ይፋዊ ቀጠሮ አለመያዙን የኋይት ሀውስ ባለስልጣናት አመልክተዋል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ