ጥቅምት 11 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) የተለያዩ ተቋማት የአሰራር ስርዓታቸውን ወደ ዲጂታል እየቀየሩ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎትም የመድሃኒት አቅርቦትን ለማሻሻል ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ እና ለዚህም እንዲያግዝ የግዢ ስርዓቱን ወደ ዲጂታል ስርዓት መቀየሩን የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር ገልግሎ ገልፀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የአሰራር ስርዓቱ ላይ ክፍተቶች እንደነበሩ በመግለፅ አሁን ላይ የ19ኙንም ቅርንጫፎቹ የግዢ ስርዓት በዲጂታል ስርዓት መቀየሩን፤ በዚህም እያንዳንዱ መድሃኒት ወጪ የተደረገበትን መጠን፣ ተደራሽነቱን፣ ምን ያህል መጠን እንደሚያስፈልግ እና ሌሎችንም መረጃዎች በመያዝ ቁጥጥር ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው አስታውቀዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ ግልጸኝነት፣ ተጠያቂነት እና ፍትሃዊ ተደራሽነትን ለመፍጠር እንደሚረዳ በመግለጽ በዘንድሮ ዓመት የተለያዩ ማሻሻያዎች በመደረጋቸው ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮችን በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ትኩረት እንደተሰጠው ዶ/ር አብዱልቃድር ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት በመድሃኒት ምርቷ የጥራት ማረጋገጫ (ማቹሪቲ ሌቭል 3) ደረጃን በማግኘቷ ከሀገር ውስጥ ባለፈ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መሸጥ እንድትችል ተመራጭ የሚያደርጋትን እድል መፈጠሩን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ይህም በሀገሪቱ ያለውን የመድሃኒት አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሻሽለው አስታውቀዋል፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ