ጥቅምት 11 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ) ይህ የተገለጸው በኢትዮጵያና በሻንሲ ግዛት የኢኮኖሚ እና ንግድ ልውውጥ ትብብር ኮንፈረንስ ላይ ነው።
የኢትዮጵያ እና የቻይናን የኢኮኖሚ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ የንግድ ትብብር ኮንፈረንስ ከቻይናው የሻንሲ ግዛት ልዑካን ጋር በመዲናች አዲስ አበባ ተካሂዷል።
የብሪክስ መመስረት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ያጠናከረ ሲሆን፣ በተለይም ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታጠብቅ አድርጓታል ሲሉ በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የምስራቅ እስያ እና ፓሲፊክ ሀገራት ጉዳዮች ዳይሬክተር አምባሳደር ደዋኖ ከድር ገልጸዋል።
የሻንሲ ግዛት ምክትል አስተዳዳሪ ዋንግ ሲኦ፣ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን መልካ-ምድራዊ አቀማመጥ፣ የህዝብ ብዛት እና በቀንዱ ያላትን ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ረዘም ላለ ጊዜ አብራ መስራቷ የጋራ ተጠቃሚነትን እንደሚያስገኝ ገልጸዋል።
በቴክኖሎጂ፣ በግብርና እና በሌሎችም የንግድ ዘርፎች የሁለትዮሽ ትስስር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል። በሻንሲ ግዛት 10 የሚሆኑ ግዙፍ የቴክኖሎጂ፣ የተሽከርካሪና ሌሎች ተቋማት መኖራቸውም ተመላክቷል።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለ መኮንን በበኩላቸው፣ ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ ካገኘችው 8.3 ቢሊዮን ዶላር፤ 6 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋው ከቻይና ጋር በተደረገ ንግድ የተገኘ መሆኑን አመላክተዋል።
በተያዘው ዓመትም የኢኮኖሚ ትስስሩ እንደሚቀጥል የገለጹ ሲሆን፤ ኮንፈረንሱ በጠቅላላው ያሉ ትብብሮች እና ግንኙነቶች በምን መንገድ ሊፋጠኑና ሊሳኩ ይችላሉ በሚለው ዙሪያ ትኩረት ያደረጉ ናቸው፡፡
በኢኮኖሚና ንግድ ትብብር፤ በትምህርት፣ በግብርና፣ በቴክኖሎጂ፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ላይ የጋራ ስምምነቶች እንደሚደረጉ እና በጋራ እንደሚሰራ ተመላክቷል።
በኢትዮጵያ ከ3ሺ 400 በላይ የቻይና ኢንቨስትመንቶች መኖራቸው እና ይህም ቻይና የጀመረችው የ-Belt and Road Initiative አካል መሆኑን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዘለቀ ተመስገን አስታውቀዋል።
በእነዚህ ኢንቨስትመንቶች ከ350 ሺህ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድሎች መፈጠራቸውንም አስረድተዋል።
ዶ/ር ዘለቀ፣ ኢትዮጵያ በቀጣይ ለአልሚዎች የግብር እፎይታና ሌሎች ማበረታቻዎችን እንደምታደርግ ገልጸው፣ በሀገሪቱ በጅምር ያሉ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ መሳተፍ ጥቅሙ የጋራ እንደሆነ አረጋግጠዋል።
በዋናነት በማዕድን፣ በሪል ስቴት፣ በኢንዱስትሪ፣ በቴክኖሎጂ፣ በጨርቃጨርቅ እና ሌሎችም ዘርፎች ትኩረት እንደተሰጣቸው ተገልጿል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ